ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላይ የተመሠረተ ስኬታማ የብልፅግና ጉዞ ላይ ትገኛለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላይ የተመሠረተ ስኬታማ የብልፅግና ጉዞ ላይ ትገኛለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላይ የተመሠረተ ስኬታማ የብልፅግና ጉዞ ላይ እንደምትገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለተኛውን ሀገራዊ “የብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ(ግሪን ሞቢሊቲ) 2025” ሳምንት ዛሬ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ ከፍተዋል።
በመክፈቻ ንግግራቸውም የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ዋነኛ መሠረቱ አረንጓዴ ልማት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ያስመዘገበችውን ድል በአረንጓዴ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ዘርፍ ለመድገም እየሰራች መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም ለበካይ ጋዝ የካርቦን ልቀት ቅነሳ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር የነበረውን ቅራኔ መፍታት የሚችለው ብክለትን በሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎች ጉዞውን ሲመራ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።
ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ውይይቶች ከንግግር ባለፈ ወደ ተግባር መሸጋገር እንዳለባቸውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ውጤትና ተግባር ተኮር የመፍትሔ አካሄድን እየተከተለች መሆኗን በማንሳት፤ ብክለት ቀናሽ የአረንጓዴ እንቅስቃሴና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መስፋፋት የዚሁ ተግባራዊ ምላሽ ዋነኛው ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ፣ ወንዞችን ከብክለት በማፅዳት፣ የፌስታል ምርቶችን አጠቃቀም በመገደብና በታዳሽ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
ታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን ከንጹሕ የኢነርጂ መሠረተ ልማት በተለይ ከሃይድሮ ኤሌክትሪክ፣ ከፀሐይና ከነፋስ ኃይል ጋር ማቀናጀት፣ የካርቦን መጠንንና የኃይል ወጪዎችን ለመቀነስ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዘላቂ ትራንስፖርት ላይ ያተኮሩ ውጥኖች የካርቦን ልቀትን ለመግታት ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ በአረንጓዴ ኢንዱስትሪያላዊነት አፈጻጸም ግንባር ቀደም እንደሚያደርጋት አንስተዋል።
አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን ብክለት ቀናሽ አብዮት የሚያበረታቱ ቴክኖሎጂዎች ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ፖሊሲ አውጪዎች፣ ባለሀብቶችና ዜጎች በጋራ እየተገነባ ስላለው ዘላቂና ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ግንዛቤና ልምድ እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ በአረንጓዴ ልማት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን መንግሥት አበክሮ እየሠራ መሆኑን በማንሳት፤ ለስኬቱ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
መንግሥት ለዚህ ዓላማ ስኬታማነት ሁሌም የመሪነት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።