ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ የትራንስፖርት ዘርፍ ታሪካዊ ሽግግር ላይ ትገኛለች - ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ የትራንስፖርት ዘርፍ ታሪካዊ ሽግግር ላይ እንደምትገኝ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሁለተኛው የብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ(ግሪን ሞቢሊቲ) ዐውደ ርዕይና ፎረም 2025 ዛሬ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተከፍቷል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላይ የተመሠረተ ስኬታማ የብልፅግና ጉዞ ላይ ትገኛለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ለትውልዱ ምቹ ሀገር የማስረከብ ጉዞ በሁሉም መስክ በስኬታማነት ቀጥሏል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በርካታ ተግባራትን ማከናወኗን አንስተዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ አርአያ የሆነ ሥራ እየሠራች መሆኑን ጠቁመው፤ የትራንስፖርት ዘርፉም ታሪካዊ ሽግግር ላይ ይገኛል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ በጨመረበት እና የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ በናረበት በዚህ ወቅት፣ ወደ አረንጓዴ ትራንስፖርት መሸጋገር ለኢትዮጵያ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሚኒስቴሩ ዘርፉን ለማዘመንና አካባቢን የማይበክል ለማድረግ ባወጣው ስትራቴጂ መሠረት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።

የባቡር ትራንስፖርቱ የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉ፣ አሮጌ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገራችን እንዳይገቡ መደረጉ በተለይም ኢትዮጵያን ከዓለም ሀገራት ግንባር ቀደም ያደረጋት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተወሰደው ቆራጥ የፖሊሲ እርምጃን ጠቅሰዋል።

በኮሪደር ልማትና በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ብዝኃ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት እየተሠራ ያለውን ሥራ በስኬት አንስተዋል።

የትራንስፖርት ዘርፉ የሚመራበት ብሔራዊ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂዎች እንዲሁም የትራንስፖርት ፍኖተ ካርታ ወደ ሥራ መግባታቸውንም ገልጸዋል።

የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂና በታዳሽ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ስታንዳርድ ጸድቆ በመተግበር ላይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርት አብዮት በሦስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቅሰው፤ አንደኛው የብዙኃን ትራንስፖርት ማመላለሻን ወደ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት የማሸጋገር ጉዳይ ነው ብለዋል።

የከተማ እንቅስቃሴን ከመሠረቱ ለመለወጥ የዐሥር ዓመት የሞተር አልባ ትራንስፖርት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባቱንም በሁለተኛነት ጠቅሰዋል።

በኮሪደር ልማቱ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገድ እንዲገነባ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ መመዝገቡን አንስተዋል።

ሦስተኛው የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርትን ማስፋፋት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በ2030 በመንገዶቻችን ላይ ከዐምስት መቶ ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዲኖሩ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም