ቀጥታ፡

የሐይማኖት አባቶች ለአብሮነት መጎልበት ከመቼውም ጊዜ በላይ የላቀ ሚናቸውን እንደሚወጡ ገለጹ

ባሕር ዳር፤ ታኅሣስ 17/2018 (ኢዜአ)፡- ለሀገር ሰላም፣ ፍቅርና አብሮነት መጎልበት የላቀ ሚናችንን መወጣታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የተለያዩ የሐይማኖት አባቶች ተናገሩ።

''ዘካሪ መካሪ የሐይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላምና ልማት'' በሚል መሪ ሐሳብ ከሰሜን ጎጃም ዞን የተውጣጡ የተለያዩ የሐይማኖት አባቶች የተሳተፉበት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።




 
በዚሁ ወቅት የመድረኩ ተሳታፊዎች ለሀገር ሰላምና ልማት መጎልበት የሀገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች ሚና የላቀ መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል።
 
የሰላም ግንባታ ሂደት ያለ ሐይማኖታዊና የሞራል ዕሴቶች ስኬታማ ስለማይሆን እነዚህን ለማስጠበቅ አጠቃላይ ምዕመኑንና ወጣቶችን ማስተማር ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሐይማኖት አባቶች ሚናቸውን ይበልጥ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል

የክልሉ መንግስት ሰላምን በማፅናት ለልማት ስራዎች ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየ ነው
 
ቄስ ታዘበው ጌታሁን በሰጡት አስተያየት፤ የሰላም መታጣት በተለያዩ አካባቢዎች ሁላችንንም ዋጋ እያስከፈለን በመሆኑ ከምንም በላይ ለሰላም ዘብ መቆም ይገባናል ብለዋል።
 
የሰላም ግንባታ ከግለሰብ ጀምሮ ወደ ቤተሰብና ሀገር የሚዘልቅ በመሆኑ እያንዳንዱ ግለሰብ ስለ ሰላም አደራና ኃላፊነት ያለበት መሆኑንም አስገንዝበዋል።



 
ሼኽ ሙሐመድ አደም በበኩላቸው፤ የሰላም ጉዳይ የእያንዳንዳችን ጥረትና ትጋት ውጤት በመሆኑ ሁላችንንም ይመለከተናል ብለዋል።
 
የጥፋት እንቅስቃሴን በማውገዝና ከጥፋት እንዲመለሱ በመምከር ጭምር የሰላም ዕሴቶች እንዲጎለብቱ በተለይም የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የላቀ ሚናችንን መወጣት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።



 
የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን፤ የሐይማኖቶች ዕሴቶች ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ይቅርታንና መልካምነትን የሚሰብኩ በመሆኑ የአባቶች ትምህርት ትልቅ ትርጉም እንዳለው አንስተዋል።
 
በመሆኑም የሐይማኖት አባቶች አጥፊዎችን መክሮ በመመለስ፣ በመልካም ተግባራት የተሰማሩትን በማመሥገን ለሰላም ዕሴቶች ግንባታ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።



 
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሐይማኖት አባቶች የሰላም ጠባቂ፣ መካሪና አስታራቂ በመሆን የጀመሩትን ሥራ መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በክልሉ የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት መንግሥት ብዙ መሥራቱን አስታውሰው በቀጣይም አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአንጻሩ የሰላም ጥሪ በመግፋት በጥፋት የሚቀጥሉ አካላት ላይ መንግሥት የተጠናከረ ርምጃ በመውሰድ ሕግ የሚያስከብር መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም