ቀጥታ፡

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሐይማኖት አባቶች ሚናቸውን ይበልጥ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል

ባሕርዳር፤ ታህሳስ 17/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው የተቀናጀ ርብርብ የሐይማኖት አባቶች ሚናቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።

''ዘካሪ መካሪ የሐይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላምና ልማት'' በሚል መሪ ሀሳብ ከሰሜን ጎጃም ዞን ከተውጣጡ የሐይማኖት አባቶች ጋር በባሕር ዳር ከተማ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ በማሕበረሰባችን የሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የሐይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በክልሉ ሰላምን ለማፅናት በሕብረተሰቡ የተቀናጀ ተሳትፎ ሲከናወን በቆየው ተግባር ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታትም ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ አርሶ አደሩንና ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉባቸው የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን አንስተዋል።

በዚህም የተገኘውን አበረታች ውጤት በማስጠበቅ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ቅንጅታዊ ስራ በተለይ የሐይማኖት አባቶች ሚናቸውን ይበልጥ አጠናክረው መቀጠል እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን በበኩላቸው እንዳሉት፤ ቀደም ሲል በአካባቢው የነበረው ችግር ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል።

ይህን ለመቀልበስ በተወሰደው የሕግ የበላይነት የማስከበር ተግባር ሰላምን ማስፈን መቻሉን አውስተዋል።

የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማፅናት የሐይማኖት አባቶች ድጋፋቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም