ቀጥታ፡

የክልሉ መንግስት ሰላምን በማፅናት ለልማት ስራዎች ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየ ነው

ባሕርዳር ፤ ታህሳስ 16/2018 (ኢዜአ) ፡- የክልሉ መንግስት ሰላምን በማፅናት ለልማት ስራዎች ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየ መሆኑን የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር፤ አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባዔ በባሕርዳር ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ጉባዔ መካሄድ ጀመረ

ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት  የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ  ፋንቱ ተስፋዬ፤ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በቅርቡ የተፈራረመው የዘላቂ ሰላም ስምምነት በክልሉ ሰላምን ለማፅናት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የክልሉ መንግስት ችግሮችን በውይይትና በንግግር መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሲያቀርብ የነበረው የሰላም አማራጭ ፍሬ ማፍራቱን የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ግጭት  ይብቃ ብለው የክልሉን መንግስት የሰላም ጥሪ ተቀብለው ለተመሰሉ የቀድሞ ታጣቂዎችን ምክር ቤቱ ያመሰግናል ያሉት አፈ ጉባኤዋ ፤ ሌሎች በጫካ የቀሩ ታጣቂዎችም የሰላም ጥሪውን ተቀብለው እንዲመጡ ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል መንግስት ሰላምን በማፅናት ለልማት ስራዎች ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየ መሆኑን ገልጸው ፤ አጠናክሮ እንዲቀጥል በምክር ቤቱ በኩል አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር የሚደረግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የምክር ቤት አባላት ለመልካም አስተዳደር መስፈን፣ ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ የሚያደርጉት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት  አስገንዝበዋል።


 

በተያዘው ዓመት የሚካሄደው 7ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅና ህዝቡ በምርጫው በንቃት እንዲሳተፍ የምክር ቤት አባላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

ምክር ቤቱ የክልሉን ትምህርት ቢሮ የ5 ወራት እቅድ አፈፃፀምና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በተከናወኑ የፋይናንስ ህጋዊነትና ክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ላይ እንደሚመክር ከመርሃ ግብሩ መረዳት ተችሏል።

በጉባዔው ልዩ ልዩ አዋጆችና ሹመቶች እንደሚጸድቁም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም