በአፍሪካ ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ ከግብጽ ሞሮኮ ከማሊ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ ከግብጽ ሞሮኮ ከማሊ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ ዛሬ በምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ይመለሳል።
በምድብ አንድ ግብጽ ከደቡብ አፍሪካ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአጋዲር ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ግብጽ ዚምባቡዌን፣ ደቡብ አፍሪካ አንጎላን በተመሳሳይ 2 ለ 1 አሸንፈዋል።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለስድስተኛ ጊዜ ነው።
እ.አ.አ በ1996 ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው 20ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው ግብጽ በአህመድ ኤል-ካስ ጎል 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ቡድኖቹ በአፍሪካ ዋንጫ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ግብጽ እ.አ.አ በ2019 ባዘጋጀችው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ በጥሎ ማለፉ በቴምቢንኮሲ ሎርች ግብ 1 ለ 0 በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ አልፋለች።
በአጠቃላይ በአፍሪካ ዋንጫው አምስት ጊዜ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ሁለቱም በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
ጠንካራ ፉክክር በሚጠበቅበት በዛሬው ጨዋታ ያሸነፈው ቡድን ወደ ጥሎ ማለፍ መግባቱን ያረጋግጣል።
በዚሁ ምድብ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ አንጎላ እና ዚምባቡዌ በማራካሽ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በተያያዘም በምድብ አንድ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
አዘጋጇ ሞሮኮ ከማሊ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ጨዋታዋን ታደርጋለች።
ሞሮኮ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ ኮሞሮስን 2 ለ 0 አሸንፋለች። በአንጻሩ ማሊ ከዛምቢያ ጋር አቻ ተለያይታለች።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ቱኒዚያ እ.አ.አ በ2004 ባዘጋጀችው 24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው ሞሮኮ 4 ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፋለች።
በዛሬው ጨዋታ ሞሮኮ ካሸነፈች ጥሎ ማለፉን ትቀላቀላለች። ማሊ በውድድሩ የመጀመሪያ ድሏን ለማስመዝገብ ትጫወታለች።
በምድብ አንድ ሌላኛው መርሃ ግብር ዛምቢያ ከኮሞሮስ ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።