ቀጥታ፡

የአፍሪካ ዋንጫ እውነታዎች

የአፍሪካ ዋንጫ ከተጀመረ ወደ ሰባት አስርት ዓመታት ገደማ አስቆጥሯል። አህጉራዊው የእግር ኳስ መድረክ የተጀመረው እ.አ.አ በ1957 ነው።

የአፍሪካ ዋንጫን ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ያሉ እውነታዎችን እንመልከት

የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ1957 ሲጀመር ተሳታፊ ሀገራቱ ሶስት ብቻ ነበሩ።  እነሱም አዘጋጇ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ናቸው። ግብጽ በፍጻሜው ጨዋታ ኢትዮጵያን 4 ለ 0 በማሸነፍ ታሪካዊውን ዋንጫ አንስታለች። ሶስቱ ሀገራት የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ሀገራት በመሆን ሁሌም በታሪክ ይወሳሉ። ከእ.አ.አ 2019 የአፍሪካ ዋንጫ አንስቶ 24 ሀገራት እየተሳተፉ ይገኛል።


 

በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ግብጻዊው ራፋት አቲያ ነው። አቲያ ግቧን ያስቆጠረው ግብጽ ሱዳንን 2 1 ባሸነፈችበት የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ነው።

ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ አንስቶ እስከ አሁን ለ11 ጊዜ ተሳትፋለች። ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የተሳተፈችው እ.አ.አ በ2021 ካሜሮን ባዘጋጀችው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1962 ያዘጋጀችውን ሶስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በማንሳት ብቸኛ ድሏን አስመዘግባለች። በፍጻሜው ጨዋታ ግብጽን 4 ለ 2 በመርታት ዋንጫውን ከፍ አድርጋለች። የፍጻሜውን ጨምሮ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው አጥቂው መንግስቱ ወርቁ የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል። በወቅቱ የኢትዮጵያ አጥቂ የነበረው ሉቺያኖ ቫሳሎ እና የግብጹ ባደዊ አብደል ፋታህ በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆነው አጠናቀዋል።

ኢትዮጵያ ሶስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ያስተናገደች ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ ውድድሩን ያዘጋጀችው እ.አ.አ በ1976 የተካሄደውን 10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ነው። በፍጻሜው ሞሮኮ ጊኒን በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።


 

ግብጽ የአፍሪካ ዋንጫን በማንሳት ስኬታማዋ ሀገር ናት።

በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ግብ ያስቆጠረ በእድሜ ትልቁ ተጫዋች የግብጹ ሆሳም ሀሰን ነው። ግብጽ እ.አ.አ በ2006 ባዘጋጀችው 25ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን 4 ለ 1 ስታሸነፍ ሆሳም ሀሰን በ39 ዓመት እድሜ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ሆሳም ሀሰን በአሁኑ ሰዓት የግብጽ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ነው።

በአፍሪካ ዋንጫ በእድሜ ትንሹ ግብ አስቆጣሪ የጋቦኑ ሺቫ ንዚጉ ነው።  ጋና እና ናይጄሪያ እ.አ.አ በ2000 በጣምራ ባዘጋጁት 22ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሀገሩ በደቡብ አፍሪካ 3 ለ 1 ስትሸነፍ ብቸኛውን ግብ በ16 ዓመቱ ከመረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል። በአፍሪካ ዋንጫ የተሰለፈ በእድሜ ትንሹ ተጫዋችም ነው።

የአፍሪካ ዋንጫ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ካሜሮናዊው ሳሙኤል ኢቶ ሲሆን 18 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል።

በአፍሪካ ዋንጫው ለበርካታ ጊዜ የተሰለፉ ተጫዋቾች ካሜሮናዊው ሪጎበርር ሶንግ እና ጋናዊው አንድሬ ዴዴ አየው ሲሆኑ በተመሳሳይ 36 ጨዋታዎችን አድርገዋል።

የአፍሪካ ዋንጫ ካዘጋጁ ሀገራት መካከል ዘጠኙ ዋንጫውን በሀገራቸው አስቀርተዋል። ይህ የአዘጋጅነት ጥቅም የሚያስገውን ውጤት ያሳያል።


 

በመጀመሪያዋ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋ ዋንጫ ያነሳችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ናት። ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1968 ባዘጋጀችው ስድስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ (በቀድሞ ስሟ ዛየር) በፍጻሜው ጋናን 1 ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜ ደርሳለች።

የአፍሪካ ዋንጫን ፈጣኗን ግብ ያስቆጠረው ግብጻዊው ሀሰን ኤል ሻዝሊ ነው። ጋና እ.አ.አ በ1963 ባዘጋጀችው አራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሻዝሊ ዛምቢያ ላይ በ23ኛው ሴኮንድ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን ክብረ ወሰኑ እስከ አሁን አልተሰበረም።

የግብጹ ግብ ጠባቂ ኢሳም ኤል ሃዳሪ እ.አ.አ በ2017 በተካሄደው 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በ44 ዓመቱ በመሰለፍ በእድሜ አንጋፋው ተጫዋች ሆኗል።

በአፍሪካ ዋንጫው 17 ተጫዋቾች ሀትሪክ ሰርተዋል። ግብጻዊው መሐመድ ዲያብ አል-ታር በመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ሀገሩ በፍጻሜው ኢትዮጵያን ስታሸንፍ የመጀመሪያውን ሀትሪክ ሰርቷል።

ግብጻውያኑ አህመድ ሀሰን እና ኢሳም ኤል ሃዳሪ በተመሳሳይ አራት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን በማንሳት ለበርካታ ጊዜ ዋንጫውን ያነሱ ተጫዋቾች ናቸው።

የግብጹ ሀሰን ሺሃታ እና የጋናው ቻርልስ ግያምፊ በተመሳሳይ ሶስት ጊዜ ውድድሩን በማሸነፍ ስኬታማ አሰልጣኞች ናቸው።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም