የአፍሪካ ዋንጫ እና ሽልማቱ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ዋንጫ እና ሽልማቱ
የአፍሪካ ዋንጫ ሽልማት ለአህጉሪቷ እግር ኳስ ልማት ያለው መልካም አንድምታ፡-
የአፍሪካ ዋንጫ የአህጉሪቷ ግዙፍ የስፖርት መድረክ ነው።
የአፍሪካ ዋንጫ በተሳታፊ ሀገራት ብዛት፣ በፉክክር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው እይታ እያደገ ይገኛል።
ይህም ውድድሩን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾች እንዲያዩት እና ውድድሩን ስፖንሰር የማድረግ ፍላጎት እንዲያድግ ምክንያት ሆኗል።
35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል።
በውድድሩ 24 ሀገራት እየተሳተፉ ይገኛል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ለውድድሩ ተሳታፊ ሀገራት በርካታ ገንዘብ ለመሸለም ተዘጋጅቷል።
ዋንጫ የሚያነሳው ሀገር የ10 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያገኛል።
የአሸናፊ ሽልማት እ.አ.አ በኮትዲቭዋር ከተካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሰባት ሚሊዮን ዶላር ሽልማት የ43 በመቶ ብልጫ አለው።
ሁለተኛ የሚወጣው አገር የ4 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ይበረከትለታል።
በግማሽ ፍጻሜው የወደቁ ሁለት አገራት እያንዳንዳቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር፤ በሩብ ፍጻሜው የተሰናበቱ አራት አገራት እያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ያገኛሉ።
በጥሎ ማለፉ ለሚሰናበቱ ስምንት ሀገራት እያንዳንዳቸው የ800 ሺህ ዶላር ሽልማት ይሰጣቸዋል።
በምድባቸው ምርጥ ሶስተኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ ሁለት ሀገራት በተመሳሳይ 700 ሺህ፣ በየምድባቸው አራተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ስድስት ሀገራት እያንዳንዳቸው የ500 ሺህ ዶላር ሽልማት ይበረከትላቸዋል።
24ቱም ተሳታፊ ሀገራት በውድድሩ ላይ እንደሚያስመዘግቡት ውጤት የሽልማቱ ተቋዳሽ ይሆናሉ።
የአፍሪካ ዋንጫን የሚያሸንፈው ሀገር በአጠቃላይ 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ሊያገኝ ይችላል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ዘንድሮ ያዘጋጀው ሽልማት እ.አ.አ በ2021 በካሜሮን አስተናጋጅነት ከተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጋር ሲነጻጸር የ40 በመቶ ብልጫ አለው።
የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ (ዶ/ር) በአፍሪካ ዋንጫ እና በሌሎች የአፍሪካ ውድድሮች ላይ የታየው የሽልማት መጠን ማደግ በአህጉሪቷ እግር ኳስ የፋይናንስ እድገት የሚያሳይ እና የአፍሪካን የእግር ኳስ ምህዳር እንደሚደግፍ አመልክተዋል።
ሽልማቱ ለአፍሪካ እግር ኳስ ልማት፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እና የእግር ኳስ ባለድርሻ አካላትን የሚደግፍ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ዋንጫ ሽልማት በአህጉራት ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ በሽልማት መጠኑ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር (ዪኤፋ) ለአውሮፓ ዋንጫ የ360 ሚሊዮን ዶላር አጠቃላይ ሽልማት የሚያዘጋጅ ሲሆን አሸናፊው ሀገር 30 ሚሊዮን ዶላር ያገኛል።
ኮፓ አሜሪካ (ደቡብ አሜሪካ) አጠቃላይ ሽልማት 72 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው። አሸናፊው ሀገር 16 ሚሊዮን ዶላር ይወስዳል።
የአፍሪካ ዋንጫ ሽልማት ከእስያ ዋንጫ እና የሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ (ኮንካካፍ) ይበልጣል።
እስያ ዋንጫ አጠቃላይ ሽልማቱ 15 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ውድድሩን የሚያሸንፈው ሀገር አምስት ሚሊዮን ዶላር ያገኛል።
ኮንካካፍ አጠቃላይ ሽልማት 15 ሚሊዮን የአሜሪካን ሚሊዮን ዶላር ነው። ዋንጫውን የሚያነሳው ሀገር የአምስት ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ይበረከትለታል።
የአፍሪካ ዋንጫ የገንዘብ ሽልማት እድገት ከአህጉሪቷ አልፎ ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሳበ ጉዳይ ሆኗል።
የገንዘብ ሽልማቱ ከጥቅም ባለፈ ለሀገራት የኢኮኖሚ ጠቃሜታዎችን የሚያስገኝ ነው።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የአፍሪካ ዋንጫ ሽልማት ለአፍሪካ እግር ኳስ ልማት ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ነው።