ቀጥታ፡

በክልሉ የመማር ማስተማር ስራውን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ባሕርዳር፤ ታሕሳስ 16/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የመማር ማስተማር ስራውን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር፣ አምስተኛ ዓመት የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ጉባዔ መካሄድ ጀመረ

የክልሉ መንግስት ሰላምን በማፅናት ለልማት ስራዎች ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየ ነው

የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን ወርቅነህ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመለከቱት፤ በክልሉ በትምህርት ዘመኑ ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ከ7 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል።


 

ይህንኑ የመማር ማስተማር ስራን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸው፤ በመማር ላይ የሚገኙት ተማሪዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

ለመማር ማስተማር ስራው ከ36 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ የመማሪያና የማስተማሪያ መፅሐፍት ታትመው መሰራጨታቸውን ገልጸዋል።

በአንድ ሺህ 107 ትምህርት ቤቶች 255ሺህ 367 ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም 157 ትምህርት ቤቶችን በአዲስ በመገንባት፣ ሁለት ሺህ 468 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን እና ከ13ሺህ 800 የሚበልጡ ነባር የመማሪያ ክፍሎችን በመጠገን ለአገልግሎት መብቃታቸውንም አብራርተዋል።

የክልሉን የትምህርት ስራ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እየተከናወኑ በሚገኙት ተግባራት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለምክር ቤቱ በቀረበው የክልሉ የ2018 የትምህርት ዘመን 5 ወራት የትምህርት አፈፃፀም ሪፖርት ዙሪያ ምክክር እየተደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም