የኢትዮጵያ መንግሥት ለኤርትራ ያቀረበው የሠላም ጥሪ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አዎንታዊ ድጋፍ እያገኘ ነው -ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

3941

አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 የኢትዮጵያ መንግሥት ለኤርትራ መንግሥት ያቀረበው የሠላም ጥሪ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አዎንታዊ ድጋፍ እያገኘ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ መለስ እንዳሉት ሁለቱ አገሮች በቀጠናው ሠላም እንዲሰፍን የጀመሩት ጥረት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ድጋፍ እየተቸረው ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣  የአፍሪካና የአውሮፓ ኅብረቶችን  ጨምሮ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ዲፕሎማቶች ድጋፋቸውን እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

”መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ሠላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ ይህም በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ ድጋፍ እየተገኘበት መሆኑን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ሰሞኑን ሲካሄድ የቆየው የኢጋድ ስብሰባ በተሳካ መንገድ መጠናቀቁን አንስተዋል።

በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ዘንድ ዘላቂ እርቅ እንዲመጣ ኢትዮጵያ በኢጋድ በኩል ለአንድ ዓመት ያህል የማደራደር ሥራዎችን ስታከናውን ቆይታለች።

እንደ አቶ መለስ ገለጻ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥረት ከሁለት ዓመት በኋላ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪርና ተቀናቃኛቸው ዶክተር ሪክ ማቻር ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲጨባበጡና እንዲወያዩ መደረጉ በማህበራዊ ሚዲያው ቀልብ ስቦ ነበር።

የኢጋድ መሪዎች ባሳለፉት ውሳኔ መሰረት ዶክተር ሪክ ማቻር ከደቡብ አፍሪካ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በሠላም ጥረቱ  በአካል እንዲሳተፉ ወስነዋል።

በዶክተር ሪክ ላይ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲነሳ መሪዎቹ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

እልባት ያላገኙ ጉዳዮችን በቀጣይ በሞሪታንያ ዋና ከተማ ኑዋሾት ከሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 31ኛው ስብሰባ በተጓዳኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተገናኝተው ለመፍታት መስማማታቸውን ጠቁመዋል።

የሠላም ሂደቱን በሚጥሱ አካላት ላይ የሚወሰደውን እርምጃ በተመለከተ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ መወሰኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና ዶክተር ሪክ ማቻር በናይሮቢ ተወያይተው የደረሱበትን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

በሌላ ዜና  ከ 36 በላይ የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች የተወከሉበት የልዑካን ቡድን  ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ጠቁመው ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከሰኔ 11 እስከ 21 ቀን 2010 ዓ ም  በጅቡቲ ጉብኝት እንደሚያደርግ ያብራሩት ቃል አቀባዩ ይህም  ሁለቱ አገሮች ያላቸውን ጠንካራ ወዳጅነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያግዝ አብራርተዋል።