የኢትዮጵያና ኤርትራን ግንኙነት ለማሻሻል የታየውን አዎንታዊ ለውጥ የአፍሪካ ህብረትና ተመድ አደነቁ

68
አዲስ አበባ ሰኔ 14/2010 የኢትዮጵያና ኤርትራን ግንኙነት ለማሻሻል የታየውን አዎንታዊ ለውጥ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አደነቁ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃማት የኢትዮጵያና ኤርትራን ግንኙነት ለማሻሻል በሁለቱም አገሮች ዘንድ የታየው አዎንታዊ ለውጥ አደነቁ። ህብረቱ የሁለቱን አገሮች የሰሞኑን የሰላም እንቅስቃሴ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ የህብረቱ ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሃማት ሁለቱ አገሮች የጀመሩት ግንኙነት የሚደገፍና የሚደነቅ ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሁለት ሳምንታት በፊት የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትናንት በኤርትራ ቴሌቪዥን ቀርበው ከኢትዮጵያ ጋር “ገንቢ ውይይት” ለመጀመር ወደ አዲስ አበባ ልዑካን ቡድን እንደሚልኩ አሳውቀዋል። ሙሳ ፋቂ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ  "ለዚህ ውሳኔ መድረሳቸው የሚበረታታ ነው" ብለዋል። ''የሁለቱም አገሮች ስምምነት በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም፣ ደህንነት፣ ብልጽግናና ውህደት ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ሚና ይኖረዋል" ብለዋል ሊቀመንበሩ። የሁለቱ አገሮች ለዚህ ደረጃ መብቃት ህብረቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 ግጭትና ጦርነት በአፍሪካ እንዲያበቃ ለማድረግ የተያዘውን  ዕቅድ እንዲሳካ ያግዛል። ሁለቱም አገሮች ወደ ዘላቂ ሰላም ለመምጣት በሚያደርጉት ጥረት ህብረቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጹን ከህብረቱ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። በተመሳሳይ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው ከደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት በዝምታ የቆየው የኢትጵያና የኤርትራ መንግስታት እርቀ ሰላም ለማውረድ የጀመሩትን ጉዞ ማድነቃቸውን ተመድ በመግለጫው አመልክቷል። አገሮቹ የአልጀርሱን የድንበር ስምምነት ተቀብለው ወደ ሰላምና አንድነት መምጣታቸው ለቀጠናው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ የላቀ ሚና ይኖረዋል። አንቶኒቶ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያና ኤርትራ እርቀ ሰላም ማውረዳቸው በመካከላቸው ያለውን ዘላቂ ሰላም ከማረጋገጥ ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ የሚኖረውን ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ሁለቱ አገሮች ለሰላምና ለአንድነትት ለሚያደርጉት ጉዞና እርምጃ ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ዋና ጸሃፊው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም