የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርና የተቃዋሚ መሪ ሬክ ማቻር ተገናኙ

94
አዲስ አበባ ሰኔ13/2010 የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያሪዲትና የተቃዋሚው መሪ ዶክተር ሬክ ማቻርን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፊት ለፊት አገናኝተው እንዲጨባበጡ አደረጉ። ሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አዲስ አበባ ውስጥ ሲገናኙ ከሁለት ዓመት በኋላ ይህ የመጀመሪያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሁለቱን ተቀናቃኞች በብሄራዊ ቤተ መንግስት እራት እንደሚጋብዟቸው ታውቋል። ከዚህ ቀደም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የደቡብ ሱዳን ተደራዳሪዎች በአካል ተገናኝተው እንዲወያዩ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። ነገ በሚካሄደው የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ስብሰባ የወቅቱ የኢጋድ ሊቀ መንበር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ የአባል አገሮቹ መሪዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር  ሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ያላቸውን ልዩነት ለማጥበብ እንዲችሉ ያስገነዝቧቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ተደራዳሪዎቹ ለሰላም ዕድል በመስጠት የህዝባቸውን ስደት፣ ሞት፣ መፈናቀልና እንግልት ለማስቆም እንዲሰሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም