አዲስ ስፖርት ፓርክ ለአትሌቶች የሚገባው ክብር የተሰጠበት ታሪካዊ ስራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ ስፖርት ፓርክ ለአትሌቶች የሚገባው ክብር የተሰጠበት ታሪካዊ ስራ ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፡-የአዲስ ስፖርት ፓርክ፣ ለሀገር ክብር የደከሙ ጀግኖች አትሌቶችን የሚዘክርና ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ተነሳሽነት የሚፈጥር መሆኑን አትሌቶች ገለጹ።
አዲስ ስፖርት ፓርክ ጀግኖችን ያከበረ ማዕከል ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲስ ስፖርት ፓርክን ትናንት መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም መርቀው ለህዝብ ክፍት አደርገዋል።
በዚሁ ወቅትም የአዲስ ስፖርት ፓርክ የመዲናዋን ዕድሳት በማፋጠን የዜጎችን ክብር ለመመለስ የተገባው ቃል መተግበሩን አንዱ ማረጋገጫ እንደሆነ ገልጸዋል።
በአምስት ነጥብ ሰባት ሄክታር መሬት ላይ ባረፈው ፓርክም በዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያን ክብር ያጎናጸፉ 15 ጀግና አትሌቶች ሐውልት ቆሞላቸዋል።
ለተተኪ ትወልድ በትዕምርትነት የሚያገለግለው ፓርክ ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ደረጃን ያሟሉ ዘመናዊ የመዋኛ ገንዳ፣ የእግርና የቅርጫት ኳስ፣ የቴኒስና የሩጫ ትራክና ሜዳዎችን የያዘ ማዕከል ነው።
በአዲስ ስፖርት ፓርክ ሐውልት የቆመላቸውና በምርቃቱ ላይ የታደሙ አንጋፋና ወጣት አትሌቶች ፓርኩ መገንባቱ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በሰጠው አስተያየት፤ ቀደም ሲል በውጭ ሀገራት የሚያዩዋቸውን መሰል ዘመናዊ ስፍራዎች ሀገር ውስጥ ተገንብቶ በማየቱ ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል ብሏል።
አዲስ አበባን ሳቢ በማድረግ በምሽት ጭምር አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጿል።
በዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ መድረክ የሀገራቸውን ክብር ከፍ ላደረጉ ጀግና አትሌቶች የመታሰቢያ ሐውልት መቆሙም ከፍተኛ ኩራት እንደተሰማው በመግለፅ፤ ለዚህም ምስጋና አቅርቧል።
አትሌት ገዛኸኝ አበራ እንደገለጸው፤ በእነርሱ ዘመን ያልነበሩ ዘመናዊ የሩጫ ትራኮች አሁን ላይ በስፋት መገንባታቸው የተተኪ ስፖርተኞችን ችግር ያቃልላል።
መንግሥት ለአትሌቶች በሰጠው ክብር አመስግኖ፣ ኢትዮጵያ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚያስችሏት የመሠረተ ልማት ሥራዎች መከናወናቸው የሚደነቅ መሆኑን ተናግሯል።
ኢትዮጵያ በሰራቻቸው የስፖርት ፓርክና የኮሪደር ልማት በሌሎች አገራት አድናቆት እያገኘች መምጣቷንም ገልጿል።
"በህይወት እያለሁ ታሪኬን የሚዘክር ሐውልት በመቆሙ ዳግም እንደተወለድኩ ሆኖ ተሰምቶኛል" ያለው ኮማንደር አትሌት ታምራት ቶላ፤ ለመንግስት ምስጋናውን አቅርቧል።
አሁን ላይ በስፋት የተገነቡ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የመሮጫ ትራኮችን ወጣቱ በአግባቡ በመጠቀም የሀገሩን ስም እንዲያስጠራ አትሌቱ ጥሪ አቅርቧል።
ኮማንደር አትሌት ሰለሞን ባረጋም በኦሎምፒክ መድረኮች ብቻ የሚታዩ ጥራት ያላቸው ስራዎች በሀገሩ በመገንባታቸው የተሰማውን ኩራት ገልጿል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ያላትን ፀጋ አልምቶ ለመጠቀም መንግስት የጀመረው ስራ ታላቅ ተምሳሌት መሆኑን አትሌቶቹ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን በበኩሉ፤ መንግስት ለስፖርት ማዘውተሪያዎች የሰጠው ትኩረት ለዘርፉ ዕድገት አዲስ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል።
እንደ አደይ አበባ ስታዲየም እና አዲስ ስፖርት ፓርክ ያሉ ግዙፍ ግንባታዎች ኢትዮጵያ የዓለም ሻምፒዮናዎችን በልበ ሙሉነት እንድታስተናግድ የሚያስችሏት መሆኑንም ጠቁሟል።
ይህ በምሽትም ጭምር የሚያገለግለው ዘመናዊ መሰረተ ልማት አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ይበልጥ ተስማሚና ሳቢ ከማድረጉም በላይ ለስፖርቱ እድገት አዲስ ተስፋ የፈነጠቀ መሆኑንም ተናግሯል።