ቀጥታ፡

አዲስ ስፖርት ፓርክ ጀግኖችን ያከበረ ማዕከል ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፡-በአዲስ አበባ ዑራኤል አካባቢ የተገነባው የአዲስ ስፖርት ፓርክ የስፖርቱን ዘርፍ የዘመናት መሻት እውን ያደረገ ድንቅ የሥራ ውጤት ሆኗል።

አዲስ ስፖርት ፓርክ ለአትሌቶች የሚገባው ክብር የተሰጠበት ታሪካዊ ስራ ነው

የአዲስ ስፖርት ፓርክም ስሙ ብቻ ሳይሆን ይዘቱም አዲስ ነው። ኢትዮጵያ ለጀግኖቿ ያላትን ክብር የገለጸችበት፣ለተተኪዎቿም የተስፋ ብርሃን የለኮሰችበት የስፖርት አውድ ለመሆን በቅቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም መርቀው የከፈቱት ይህ ፓርክ፣ የመወዳደሪያ ስፍራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ ልማት ጉዞ እንደሚያሳይ ተገልጿል።

በፓርኩም የስፖርት መሠረተ ልማት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ በአንጸባራቂ ድሎቻቸው ያውለበለቡ ድንቅ የአትሌቲክስ ፈርጦች ሐውልት ቆሟል።

በዚህ ታሪካዊ ስፍራ ሐውልት ከቆመላቸው 15 የኢትዮጵያ እንቁ አትሌቶች መካከል ስድስቱ እንስት ጀግና አትሌቶች ሃሳባቸውን አጋርተውናል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፈር ቀዳጇ አትሌት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፤ ፓርኩን ስትመለከት የታያት የሀገር ከፍታ ነው። "እንዲህ ዓይነት ፓርክ በውጭ ሀገር ስንመለከት እንመኘው ነበር፤ ዛሬ በሀገራችን ተሰርቶ ማየቴ ታላቅ ደስታ ነው" ትላለች።


 

አትሌት ደራርቱ አክላም፣ ፓርኩ የኢትዮጵያን የኦሎምፒክ ተሳትፎ እንደሚለውጥ ገልጻ፤ "እኛ በባዶ እግር ነው የጀመርነው፤ አሁን ግን መሰረተ ልማት ተሟልቶ በፕሮፌሽናል ደረጃ መሰልጠን ተችሏል።እንዲህ ያሉ ስራዎች ከተጠናከሩ 15 ሳይሆን 15 ሺህ ወርቅ እናመጣለን" ስትል ለወደፊቱ ትውልድ ያላትን ትልቅ ተስፋ አጋርታለች።

የማራቶን ድል አድራጊዋ አትሌት ኮማንደር ፋጡማ ሮባ፣ በፓርኩ ውስጥ የቆመው ሐውልት ትርጉም በቃላት የማይገለጽ መሆኑን ትናገራለች።


 

"ሐውልታችን መቆሙ ለእኛም ሞራል ለሚቀጥለው ትውልድም ትምህርት ነው" የምትለው ፋጡማ፣ይህ ስፍራ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ የስኬት ማስታወሻ መሆኑን ገልጻለች።

በውጭ ሀገራት የምናያቸው ጥራት ያላቸው የስፖርት ፓርኮች ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ላይ መገንባታቸው ለስፖርቱ እድገት አቅም እንደሚሆንም አብራርታለች።

የረጅም ርቀት ንግሥቷ ኮማንደር ጥሩነሽ ዲባባ፣የሐውልቱን መቆም ከሀገር ክብርና ከትውልድ ቅብብሎሽ ጋር አስተሳስራዋለች።


 

ድሮ እኛ በነባር አትሌቶች ተነሳስተን ነው እዚህ የደረስነው የምትለው ደማቋ አትሌት፥ ዛሬ ደግሞ ተተኪዎች የእኛን ሐውልት ሲያዩ ለታላቅነት መነሳሳት ይፈጥርላቸዋል ትላለች።

ጀግኖችን በሕይወት እያሉ ማክበር ለሚመጣው ትውልድ ለሀገሩ ትልቅ ሥራ እንዲሠራ መነሳሳት የሚፈጥርና ምሳሌ እንደሚሆንም በኩራት ገልጻለች።

ለአትሌት መሰረት ደፋር አዲስ ስፖርት ፓርክ ማመን እስኪያቅታት ነው የሆነባት።


 

"ቃላት ያጥረኛል" የምትለው አትሌቷ፤ ኡራኤል አካባቢን በዚህ ገጽታ አየዋለሁ ብዬ አላመንኩም በማለት ነበር ስሜቷን የገለጸችው።

አትሌት መሰረት ቀደም ሲል በአዲስ አበባ መሮጫ ስፍራ እንኳን እንዳልነበረ አስታውሳ፤ አሁን ግን ህዝቡ ጤናውን የሚጠብቅበት ውብ ቦታ መዘጋጀቱን ታደንቃለች።

አልባሌ ቦታ ከመዋል እዚህ መጥቶ ሀገርን ለማስጠራት መስራት ይገባል በማለትም ለወጣቶች ጥሪዋን አስተላልፋለች።

አትሌት ሃምሳ አለቃ አልማዝ አያና በበኩሏ የፓርኩን ጥራትና ምሉዕነት አድንቃለች።


 

"ምንም እንከን የሚወጣለት ነገር የለም፤ ይህ ልዩ ነው" የምትለው አትሌት አልማዝ፣ፓርኩ ስፖርት አቁመው የነበሩትን እንኳን ዳግም ወደ ሜዳ እንዲመለሱ የሚያደርግ እንደሆነ ትገልጻለች።

በመንግሥት ለስፖርት ዘርፉ የተሰጠ ትልቅ ሥፍራ መሆኑንም ትመሰክራለች።

አትሌት መቶ አለቃ ቲኪ ገላና ፓርኩ ሁሉንም ስፖርት በአንድ ማዕከል መያዙ ልዩ ያደርገዋል ብላለች።


 

ለሀገር አቋራጭ መሮጫ የሚሆን ስፍራ፣ የዋና፣ የእግር ኳስና ሌሎች ስፖርቶችን መሠረተ ልማት ማካተቱ ለኢትዮጵያ ስፖርት ከፍታ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁማለች።

አትሌቶቹ አዲስ ስፖርት ፓርክ የኢትዮጵያን የነገ ተስፋ በፅኑ መሰረት ላይ የጣለ ታላቅ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም