የነዳጅ አቅርቦት ጫናን ለመቋቋም መንግስት ያሳለፈውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ ምርትን በፍትሐዊነት እያከፋፈልን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ አቅርቦት ጫናን ለመቋቋም መንግስት ያሳለፈውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ ምርትን በፍትሐዊነት እያከፋፈልን ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፦የመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ሁኔታን ተከትሎ የነዳጅ አቅርቦት ጫናን ለመቋቋም መንግስት ያሳለፈውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ ምርትን በፍትሐዊነት እያከፋፈሉ እንደሚገኝ የነዳጅ ማደያዎች ገለጹ።
በነዳጅ አቅርቦት ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመቋቋም የተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በአግባቡ እንተገብራለን -አሽከርካሪዎች
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአዲስ አበባ የተለያዩ የነዳጅ ማደያዎች ባደረገው ቅኝት፤ ማደያዎቹ የሚራገፈውን ነዳጅ በፍትሐዊነት ለተጠቃሚዎች እያከፋፈሉ እንደሚገኙ ተመልክቷል።
የመካከለኛው ምስራቅ ግጭትን ተከትሎ በርካታ የዓለም ሀገራት በነዳጅ አቅርቦት ላይ የተፈጠረውን መስተጓጎል ለመቋቋም ጥብቅ የቁጠባ መመሪያዎችን በማውጣት ላይ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅታዊ ሁኔታው ሳቢያ በነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመቋቋም ዜጎች ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀሙ ማሳሰባቸው ይታወቃል።
ይህንንም ተከትሎ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የአቅርቦት ሰንሰለቱን በቁጠባና በጥብቅ ቁጥጥር መምራት የሚያስችል የተፅዕኖ መቋቋሚያ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ይፋ እንዳደረጉት፤ በነዳጅ አጠቃቀም ረገድ ለሚከተሉት ዘርፎች ቅድሚያ እንዲሰጥ መመሪያ ተላልፏል፦
በዚህም መሠረት፡-ነዳጅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች በማደያ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፤ ከፍተኛ አምራችና የኤክስፖርት ድርጅቶች በቀጥታ፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች በቀጥታ፣ የገቢና ወጪ ንግድን ጨምሮ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች ግብርናን የሚያዘምኑ ትራክተሮች፣ የከተማና ሀገር አቀፍ የብዙሃን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች እንዲሁም በናፍጣ የሚሰሩ ሌሎች ለህብረተሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያደርግ የቅድሚያ የነዳጅ አጠቃቀም አሠራር የሚተገበር መሆኑን መግለፃቸው ይታወቃል።
የገርጂ ኖክ ነዳጅ ማደያ ሥራ አስኪያጅ መልካሙ ሲያልፍ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ማደያው በመንግሥት የወረዱ መመሪያዎችን በአግባቡ በመተግበር ላይ ይገኛል።
በተለይም ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ለተወሰነላቸው ድርጅቶች ሕጋዊነታቸውን በማረጋገጥ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በካዛንቺስ የኦላ ነዳጅ ማደያ ሠራተኛ መሰረት ወንድም በበኩላቸው፤ ለኅብረተሰቡና ለሀገር ልማት ወሳኝ ለሆኑ አካላት በወጣው አሠራር መሠረት ምርቱን እያቀረቡ መሆኑን አብራርተዋል።
የሰባራ ባቡር ቶታል ነዳጅ ማደያ ሱፐርቫይዘር ባዬ መኮንን፤ ነዳጅን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በፍትሐዊነት እያከፋፈሉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ ኅብረተሰቡ ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀም፣ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን እንዲከተልና የእግር ጉዞ ባህልን እንዲያጎለብት ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም የሕዝብ ትራንስፖርትን በመጠቀምና በነዳጅ ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በማጋለጥ ረገድ ዜጎች ከመንግሥት ጋር ተባብረው እንዲሠሩ ማሳሰቡ ይታወሳል።
የማደያዎቹ የሥራ ኃላፊዎችም በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በሀገር ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ጫና ለመቀነስ ሁሉም ሰው በኃላፊነት ስሜትና በትዕግሥት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል።