ቀጥታ፡

በነዳጅ አቅርቦት ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመቋቋም የተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በአግባቡ እንተገብራለን -አሽከርካሪዎች

ሐረር ፤መጋቢት26/2018 (ኢዜአ)፡-በነዳጅ አቅርቦት ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመቋቋም የተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በአግባቡ እንተገብራለን ሲሉ  አሽከርካሪዎች ገለጹ።

በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ምክንያት በኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የተለያዩ መመሪያዎች ወጥተዋል።

በዚህም መሰረትም የችግሩን ሁኔታ ከግምት ያስገባ አሰራርን መከተልና የመፍትሄ አቅጣጫውን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል።

በሐረር ከተማ ነዳጅ በመቅዳት ላይ የነበሩ አሽከርካሪዎች ለኢዜአ  እንዳሉት በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረውን ወቅታዊ ሁኔታ ያስከተለውን የነዳጅ እጥረት ለመቋቋም መንግስት ያስቀመጠውን የመፍትሔ አቅጣጫ መተግበር የግድ ነው።

አሽከርካሪዎቹ አቶ አብዱልዋሲ ከማል እና አቶ ረታ ጊዴሳ ፤ የነዳጅ እጥረቱ በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተ በመሆኑ የተገኘውን ነዳጅ በአግባቡ በመጠቀም ችግሩን ለማለፍ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።

በመሆኑም መንግስት በከፍተኛ ድጎማና ተግዳሮቶች ውስጥ አልፎ ያቀረበውን ነዳጅ በአግባቡ በመጠቀም እና ከብክነት በመከላከል አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነን ነው ያሉት።

አቶ አሳመረ ዘሪሁን እና አቶ ልኡል ሞላ የተባሉ አሽከርካሪዎች በበኩላቸው   መንግስት የነዳጅ አቅርቦት እጥረቱን ለመቅረፍ ባወጣው የመፍትሄ አቅጣጫ መሰረት እየተጠቀሙ እንደሚገኙም ነው የሚገልጹት።

የነዳጅ አቅርቦት እጥረቱ እያለ ለተሽከርካሪዎች ባግባቡ ለማዳረስ እየተከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ ሆኖ እንዳገኙትም አስረድተዋል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሰተዳድር ሮዛ ዑመር በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የሚቀርበውን ነዳጅ በቁጠባና ትኩረት ለሚሹ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መሰረት ባደረጉ መልኩ እየተሰራጨ ነው።

በዚህም ለህዝብ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎች፣ ማሽነሪዎችና ፋብሪካዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይት ፈጽመው የተገኙ የነዳጅ ማደያዎችና ግለሰቦች በቁጥጥር ስር በማዋል  ህግን መሰረት ያደረገ  እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም