የምናከናውናቸው የልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን ማኅበራዊ ትስስር ያጠናክራሉ -ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የምናከናውናቸው የልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን ማኅበራዊ ትስስር ያጠናክራሉ -ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፡- የምናከናውናቸው የልማት ሥራዎች የከተማችንን ነዋሪዎች ማኅበራዊ ትስስር የሚያጠናክሩ ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ታላቋን ኢትዮጵያ ማለም ብቻ ሳይሆን በተግባር እንገነባታለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ከንቲባ አዳነች በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ውብና ማራኪ ተደርጎ በ1 ነጥብ 3 ሄክታር ላይ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለሕዝብ የተገነባውን የሳር ቤት ፕላዛ መርቀን ሥራ አስጀምረናል ብለዋል።
በከተማችን የምናከናውናቸው የልማት ሥራዎች ለሰው ልጅ ክብርና ጥቅም የሚሰጡ፣ የኑሮ ጫናን የሚያቃልሉ እንዲሁም የከተማችን ነዋሪዎች ማኅበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩባቸው ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
አክለውም፤ የመንግሥትን የልማት ስትራቴጂ በመከተል የግል ሴክተሩም በከፍተኛ ፍጥነትና ተነሳሽነት አብሮን እየሠራ ይገኛል ብለዋል ከንቲባዋ።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከራሱ የግል ይዞታ 1 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት በመወሰን አልምቶ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውል ማድረጉ አዲስ እሳቤና ትልቅ ለውጥ መሆኑንም አስረድተዋል።
እንዲሁም የወንዝ ዳር ልማትም ስንሠራ አብሮን የሠራ ስለሆነ በከተማችን ነዋሪዎች እና በራሴ ስም ከልብ አመሰግናለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።