ታላቋን ኢትዮጵያ ማለም ብቻ ሳይሆን በተግባር እንገነባታለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ታላቋን ኢትዮጵያ ማለም ብቻ ሳይሆን በተግባር እንገነባታለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2018 (ኢዜአ)፦ ታላቋን ኢትዮጵያ ማለም ብቻ ሳይሆን በተግባር እንገነባታለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የአዲስ አበባን እድሳት ለማፋጠን እና የዜጎቻችንን ክብር ለመመለስ የገባነውን ቃል አንዱ ማረጋገጫ የሆነውን የአዲስ ስፖርት ፓርክን በይፋ መርቀን ከፍተናል ብለዋል።
በ5 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ፕሮጀክት፤ በኦሎምፒክ መድረክ ለሀገራችን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ 15 አትሌቶችን የሚዘክሩ የክብር ሐውልቶችን በፓርኩ መሃል በማቆም፣ የጀግኖቻችን ታሪክ ለተተኪ ትውልድ ስፖርተኞች ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል ሲሉም ገልጸዋል።
የኦሎምፒክ ደረጃውን የጠበቀ የመዋኛ ገንዳ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስና የሜዳ ቴኒስ መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የ800 ሜትር የሩጫ ትራክን ጨምሮ፤ እያንዳንዱ የዚህ ማዕከል ክፍል የዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲያሟላ ተደርጎ መገንባቱንም አመልክተዋል።
የእውነተኛ ልማት ማዕከል ማህበረሰቡ ላይ መሆን አለበት በሚል እምነት፣ ይህ ፕሮጀክት ከላቀ የስፖርት አገልግሎት ባለፈ በልማቱ ምክንያት ለተነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ አቅም የሚሆኑ 105 አዳዲስ የንግድ ሱቆችን እንዲሁም 3 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ሰፊ ፕላዛ መያዙንም ነው የገለጹት።
በተጨማሪም በአንዴ 300 መኪናዎችን የሚይዝ ባለ ሁለት ወለል የምድር ቤት መኪና ማቆሚያ ያለውና ከወንዝ ዳርቻ ልማት ጋር የተሳሰረው ይህ ፓርክ፤ ንፁህና ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የጀመርነውን ቁርጠኝነት ጉልህ ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።
ታላቋን ኢትዮጵያ ማለም ብቻ ሳይሆን በተግባር እንገነባታለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።