ቀጥታ፡

ይበጀናል የምንለውን ፓርቲ ለመምረጥ ከወዲሁ የምርጫ ካርዳችንን ወስደናል - መራጮች

ጎንደር ፤ መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፦በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገር ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ የጎንደር ከተማ መራጮች ተናገሩ፡፡

የዲላ ከተማ ነዋሪዎች በጠቅላላ ምርጫው ድምፅ ለመስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ነው

የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ገበያው ተረፈ ለኢዜአ እንደገለጹት በዴሞክራሲያዊ መንገድ በምርጫ ተወዳድሮ የተመረጠ መንግስት ለሀገር እድገትና ብልጽግና መሰረት ነው። 


 

ይህን በመገንዘባቸውም ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ ቀድመው በማውጣት የምርጫውን እለት እየተጠባበቁ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ፋሲል ጀመረ በበኩሉ ምርጫ የሀገራችንን የወደፊት እጣ ፈንታ የምንወስንበት መሆኑን ሁሉም ሰው ሊገነዘብ ይገባል ሲል ገልጿል።


 

በዚህም ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው መምረጥ እንዲችሉ የምርጫ ካርድ ጊዜው ከማብቃቱ በፊት ማውጣት አለባቸው ብሏል።

ምርጫ ህዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ መሪውን ለስልጣን የሚያበቃበት በመሆኑ እኔም ባወጣሁት ካርድ የምፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ሲል ተናግሯል፡፡ 

ወይዘሮ ወርቄ ታደሰም ለሴቶች እኩልነት፣ መብትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የቆመ ፓርቲን ለመምረጥ የሚያስችለኝን የምርጫ ካርድ አውጥቻለሁ ብለዋል።


 

ካርዴንም ለህዝቡ ኑሮ መለወጥ እንዲሁም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲን በመምረጥ  እጠቀምበታለሁ ሲሉ ገልጸዋል። 

በሚዲያ እየተካሄደ ያለው ክርክር ፓርቲዎች ያላቸውን ፖሊሲና ፕሮግራም ለመገንዘብ እያስቻላቸው በመሆኑ በምርጫው እለት ድምጽ ለመስጠት እንደማይቸገሩ አስተያየት ሰጪዎች አረጋግጠዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው የጊዜ ሰሌዳ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም