የዲላ ከተማ ነዋሪዎች በጠቅላላ ምርጫው ድምፅ ለመስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲላ ከተማ ነዋሪዎች በጠቅላላ ምርጫው ድምፅ ለመስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እየወሰዱ ነው
ዲላ ፤ መጋቢት 27/2018 (ኢዜአ)፦በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እየወሰዱ መሆኑን የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውን እያስተዋወቁ ሲሆን መራጮችም የምርጫ ካርዳቸውን በመውሰድ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የበኩላቸውን ለማበርከትና ዜግነት ሀላፊነታቸውን ለመወጣት እየሰሩ ናቸው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዲላ ከተማ ነዋሪዎች፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ በመስጠት ህገ-መንግሥታዊ መብታቸውን ለመጠቀም የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ እሸቱ ፀጋዬ በምርጫው በንቃት መሳተፍ የዜግነት ግዴታቸው መሆኑን አንስተዋል።
የምርጫ ዴሞክራሲያዊነት የሚወሰነው በዜጎች ተሳትፎ ልክ በመሆኑ ለዚህም የምርጫ ካርድ በመውሰድ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ይህም በቀጣይ አምስት ዓመታት በአግባቡ ይመረኛል፣ ይጠቅመኛል ብለው ያመኑበትን ፓርቲ ለመምረጥ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
በምርጫው ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም ካርድ መውሰዳቸውን ያነሱት ደግሞ ወይዘሮ እመቤት ደበሌ ናቸው።
ምርጫ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መንግስት የሚሰየምበት መሆኑን አንስተው ለዚህም የመራጭነት ካርድ በመውሰድ መምረጥ እንደሚገባም አንስተዋል።
ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ያውቃል ሞላ በበኩላቸው፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የመራጭነት ካርድ በመውሰድ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ይህም የፈለገውን እና ያመነበትን ፓርቲ የመምረጥ መብቱን እንዲጠቀም እንደሚያስችላቸው ነው የጠቀሱት።
ምርጫው ሠላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ድምፅ በመስጠት ህገ-መንግሥታዊ መብቱን ለመጠቀም መዘጋጀቱን ያነሳው ደግሞ ወጣት ልኡል በቀለ ነው።
በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ የምርጫ ካርድ መያዝ ወሳኝ በመሆኑ የመራጭነት ካርድ መውሰዱን ተናግሮ ሌሎችም በቀሩት ቀናት ካርድ እንዲወስዱ ጠቁሟል።