ቀጥታ፡

ዜጎች በጠቅላላ ምርጫው ተሳትፏቸውን በማጠናከር የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆን አለባቸው

ዲላ፤ መጋቢት 16/2018 (ኢዜአ)፦ ዜጎች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተሳትፏቸውን በማጠናከር የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን መመዝገባቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አማራጭ ሐሳቦች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል

ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ 198 ዕጩዎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ 8 ሺህ 736 ለክልል ምክር ቤቶች ለመወዳደር የተመዘገቡ ሲሆን 73 የሚሆኑት ደግሞ በግል በዕጩነት የቀረቡ መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ዲን ፍሬዘር ዓለሙ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ህዝብ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጠው ያስተዳድረኛል ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ በምርጫ ካርዱ ሲሰይም ነው።


 

የሃሳብ ልዩነቶች የምርጫ ሂደት እድሎች በመሆናቸው ከማሸነፍና መሸነፍ በላይ የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል በመገንባት ለቀጣይ ትውልድ ሃገርን ለማጽናት የሚቻልበት መንገድ እንደሆነ አመላክተዋል።

በመሆኑም በቀጣይ አምስት ዓመት ሀገሪቱን የሚመራ ፓርቲ ወደ ስልጣን ለማምጣት ዜጎች በኃላፊነት በምርጫው ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ዴሞክራሲያዊ ምርጫ  ለዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና ጠቀሜታው የጎላ ነው ያሉት ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ- ሰብ ኮሌጅ ዲን ፕሮፌሰር ዘለቀ አርፍጮ ናቸው።


 

የመራጮች ምዝገባ ተሳትፎ፣ የፓርቲዎች አማራጭ ፖለሲዎችን የማስተዋወቅና ክርክሮችን ማድረግ እየታየ ያለው ተሳትፎ መልካም ጅማሮ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዜጎች በምርጫው የነቃ ተሳትፏቸውን በማጠናከር ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚችሉበት መንገድ መሆኑንም ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅትም በተለይ ምሁራን የፖሊሲ አማራጮችን በመተንተንና ህዝቡ በተገቢው መንገድ ግንዛቤ እንዲይዝ በማድረግ  ረገድ ሚናችንን ማጠናከር አለብን ነው ያሉት።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአካል ጉዳተኞች ክንፍ ሰብሳቢ መአዛ ሱልጣን በበኩላቸው፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አካል ጉዳተኞች በተገቢው መንገድ ተሳትፎ እያደረግን ነው ብለዋል።


 

የምርጫ ስኬታማነት የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን አንስተው ለዚህም የመራጮች ካርድ ከመውሰድ ጀምሮ በየደረጃው የሚደረገው ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም