ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አማራጭ ሐሳቦች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል

ሰመራ ፤ መጋቢት 16/2018(ኢዜአ)፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለአገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት አማራጭ ሐሳቦች ላይ ማተኮር  እንዳለባቸው በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አስገነዘቡ።

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የሚከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

በኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ ቀን ተወስኖ፣ በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የተለያዩ የቅድመ ምርጫ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ። 

ከቅድመ ምርጫ መርሃ ግብሮች መካከልም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች ስም እንዲሁም የመለያ ምልክት አደራደር ቅደም ተከተል ለመወሰን የዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓት ማካሄዱ ይጠቀሳል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹም የምርጫ ክርክር እና የቅስቀሳ መርሃ ግብሮቻቸውን እያካሄዱ መሆኑም ይታወቃል።

በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ካሳሁን አበራ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳመለከቱት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያደርጉት ክርክርና ቅስቀሳ አገርን ወደፊት በሚያስቀጥሉና ዘላቂ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባቸዋል። 


 

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገርን ጥቅም ባስቀደመና ህልውናን ባስጠበቀ መልኩ የተሻሉ አማራጭ ሐሳቦችን ይዘው መቅረብ እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ የምርጫ ሕግና ደንቦችን በአግባቡ ማክበር እንዲሁም የገቡትን ቃልና ማኒፌስቶ ተረድቶ ለሕዝብ ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል።

ለመራጩ ሕዝብ ጠቃሚ ሐሳቦችን ከማቅረብ ይልቅ፣ አንዱ በሌላው ላይ ግጭት ሊቀሰቅሱ ከሚችሉ ንግግሮች መቆጠብ እንዳለባቸውም አክለዋል።

በአጠቃላይ በምርጫ ሂደቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማጠናከር፣ የሕዝብን ድምፅና የምርጫ ውጤትን በሰላማዊ መንገድ የመቀበል ባሕል ሊዳብር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም