ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የሚከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የሚከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018(ኢዜአ)፦ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት ከባለድርሻ አካላትጋር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል ዕጩዎች ስም እንዲሁም የመለያ ምልክት አደራደር ቅደም ተከተልን ለመወሰን የተዘጋጀውን የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የምርጫ ሂደቱን በስኬት ለመምራት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበራትና ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።
በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎችን የዕጩዎች ምዝገባ በማጠናቀቅ በየምርጫ ክልሉ ዕጩዎችን ይፋ በማድረግ ለሚቀርቡ አቤቱታዎች አፋጣኝ ምላሽ እየተሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በ'ምርጫዬ' የዲጂታልና ማኑዋል አማራጭ መራጮች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን ምዝገባ እያካሄዱ መሆኑን ጠቁመው፤ በ46 ሺህ 757 የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁሶች መሰራጨቱን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆን በነፃ የአየር ሰዓት ድልድል፣ በፓርቲዎች የክርክር መድረክና በአስቻይ የፀጥታ ሁኔታዎች ዙሪያ በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
ለመራጮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለሚሰጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ተገቢውን የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በቦርዱ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ ቀነኒ ኢንሰርሙ እንደገለጹት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች ስም እንዲሁም የመለያ ምልክት አደራደር ቅደም ተከተል የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ምርጥ ተሞክሮዎች የተቀመሩበት ነው ብለዋል።
ቦርዱ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚሰፍረውን የዕጩዎች ቅደም ተከተል ለመወሰን በምርጫ ክልሎች ለ10 ቀናት የሚቆይ የዕጣ አወጣጥ ሥርዓት ያካሂዳል።