ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚጠበቅብንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚጠበቅብንን እንወጣለን
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ፓርቲያቸው የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣ የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀ መንበር አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) ገለጹ።
ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የሚከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል
የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ የምርጫ ማኒፌስቶውን ይፋ ያደረገ ሲሆን የተመሰረተበትን ሰባተኛ ዓመትም አክብሯል።
የፓርቲው ሊቀ-መንበር አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ጠንካራ ሀገር መንግሥት ለመመስረት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወሳኝ እንደሆነ ፓርቲው ያምናል ብለዋል።
በዚህም ፓርቲው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ፓርቲው ዛሬ ይፋ ያደረገው የምርጫ ማኒፌስቶ የሀገሪቱን ነባራዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ከግንዛቤ ያስገባ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ጠቅላላ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ፓርቲው የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣ ጠቁመው፤ ለዚህም አባላት የሚመሩበት የሥነ-ምግባር መመሪያ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለይላ አሊ በበኩላቸው፤ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ባለፉት ሰባት አመታት ሚዛናዊና ምክንያታዊ የፖለቲካ ዕይታን በመከተል ዛሬ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
በቀጣይ እንደ ሀገር የዴሞክራሲ ባህልን ለመገንባት እየተደረገ ባለው ጥረት የበኩሉን አሻራ እንደሚያሳርፍ አስታውቀዋል።
የፓርቲው የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ነቢሃ መሐመድ፤ ፓርቲው ትምህርት መር የልማት ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የሁሉም ነገር መነሻና መዳረሻ ትምህርት መሆኑን በመጥቀስ፣ ፓርቲው ሚዛናዊና ምክንያታዊ የፖለቲካ አካሄድ እንደሚከተል አረጋግጠዋል።