በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ከመጋቢት 18 ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት ይሰጣል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ከመጋቢት 18 ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት ይሰጣል
ወራቤ ፤ መጋቢት 15/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተቀናጀ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክትባት ከመጋቢት 18/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለፀ፡፡
በክልሉ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለማከም በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ የምርመራ ስራ እየተከናወነ ነው
ኢንስቲትዩቱ በክልሉ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻን በማስመልከት ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በወራቤ ከተማ ተካሄዷል፡፡
የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተቀናጀ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክትባት ከመጋቢት 18/2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት ይሰጣል።
በክልሉ ፖሊዮን ለመከላከል ከዚህ ቀደም በአራት ዙር በተሰራው ስራ ከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ህፃናትን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
በዚህም ፖሊዮ በህፃናት ላይ የሚያደርሰውን የጤና እክል በመከላከል የህፃናትን ተጋላጭነት መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡
በሚሰጠው 5ኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ተጠቃሚ እንደሚደረጉም ገልጸዋል።
ከፖሊዮ ክትባት ባሻገር መደበኛ ክትባትን ያቋረጡ፣ የሥርዓተ-ምግብ እጥረት፣ በተፈጥሮ የእግር ቆልማማነት፣ የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ያለባቸው ህፃናት ተለይተው ወደ ህክምና እንዲመጡ ይደረጋል ብለዋል።
ለዘመቻው ስኬታማነት የጤና ባለሙያዎችን የማሰልጠንና የግብዓት አቅርቦት ዝግጅት ስለመደረጉም አረጋግጠዋል፡፡
የሚዲያ ተቋማት የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የፖሊዮ በሽታ የሚያስከትለውን ችግር በመቀነስ ረገድ እየተወጡ ያለውን ተግባር ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።
የሀዲያ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ አቡሌ በበኩላቸው፤ የፖሊዮ በሽታ በታዳጊ ህፃናት ጤና ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ ህፃናትን በወቅቱ እንዲያስከትብ ሚዲያው የሚጠበቅበትን ሚና ይወጣል ብለዋል።
በፖሊዮ በሽታ የሚደርሰው ጫና በቀላሉ ሊታይ እንደማይገባ የተናገሩት በደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የወልቂጤ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ዘለቀ ናቸው፡፡
በሽታውን ለመከላከልም የሬዲዮ ጣቢያው በአካባቢው በሚነገሩ ቋንቋዎች እንዲሁም ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ተገቢውን ግንዛቤ እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ በክልሉ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት አመራሮችና የሁሉም መዋቅሮች የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡