በክልሉ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለማከም በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ የምርመራ ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለማከም በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ የምርመራ ስራ እየተከናወነ ነው
ሀዋሳ፤ መጋቢት 14/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለማከም በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ የምርመራ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡
ዓለም አቀፉ የቲቢ ቀን በክልል ደረጃ ''አዎ ቲቢን ማጥፋት እንችላለን'' በሚል መሪ ሀሳብ በወንዶገነት ወረዳ በምርመራና በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተከብሯል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል `ሀላፊ በላይነህ በቀለ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለማከም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዙ 12 ተንቀሳቃሽ የምርመራ ኤክስሬዎች ስራ ላይ ናቸው።
በዚህም ጥራቱን የጠበቀ የምርመራ አገልግሎት ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በ47 የምርመራ ማዕከላትና በተለያዩ የጤና ተቋማት በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ የምርመራና ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በየመዋቅሩ ያሉ የጤና አደረጃጀቶችን በመጠቀም የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ትኩረት እንደተሰጠው አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ መድሃኒት የተላመደ ቲቢን ለማከም በሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ የህክምና ማዕከል ተከፍቶ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዘርፉ የሚሰራው ሪች ኢትዮጵያ ሃዋሳ ማስተባበሪያ ቢሮ የክልሎች ክላስተር አስተባባሪ ጎሳ ግርማ በበኩላቸው ተቋሙ የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመግታት በተለያዩ አካባቢዎች እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም በቴክኖሎጂ የታገዘ የቲቢ ህመምተኞችን የመለየት፣ የማከምና ስርጭቱን የመከላከል ስራን ከመንግስት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከፕሮግራሙ ተሳታፊዎች መካከል ተገቢውን ህክምና አግኝተው ከቲቢ ነጻ የሆኑ የወንዶ ገነት ወረዳ ነዋሪዎች ወይዘሮ ብርቱኳን ሹብሻ እና ወጣት ሳሙኤል ማቲዎስ የቲቢ ምርመራና ህክምና በጤና ተቋማት በነጻ ማግኝታቸውን ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የቲቢ ምርመራና የግንዛቤ ስራ የተሰራ ሲሆን የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡