የ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ የቱሪዝም ማንሰራራትን የሚያሳይ አይን ገላጭ ፕሮጀክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ የቱሪዝም ማንሰራራትን የሚያሳይ አይን ገላጭ ፕሮጀክት ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 14/2018 (ኢዜአ)፦የ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ የቱሪዝም ዘርፉን ማንሰራራትን የሚያሳይ አይን ገላጭ ፕሮጀክት መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መሐመድ አብዱራህማን (ኢ/ር) ገለጹ።
የ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ ለአፋር ህዝብ የተሰጠ ትልቅ ክብር ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት በፍራፍሬ እና በደን ዛፎች የተከበበውን የ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
የኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ ፕሮጀክት አስተባባሪ መሐመድ አብዱራህማን (ኢ/ር) የአፋር ክልል የቱባ ባህላዊ እሴቶች እና የድንቅ ተፈጥሯዊ መስህቦችና ስልጣኔዎች መዳረሻ ነው ብለዋል።
አፋር የቀደምት ፍጥረት መገኛ እና የዓለም አስደናቂ ስፍራ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በክልሉ ካሉት ድንቅ እና ልዩ የተፈጥሮ ስጦታዎችን በዘመናዊ መልክ ለመግለጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ መገንባቱን አመልክተዋል።
የገበታ ለትውልድ አካል የሆነው ሎጅ ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ አቅጣጫ የሚገኝ እና 138 ሄክታር ላይ ያረፈ መሆኑን ጠቁመዋል።
የፍልውሃ ምንጮች እና የዘንባባ ዛፎች የአካባቢው ልዩ መገለጫዎች መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ፕሮጀክቱ የአካባቢውን እሴቶች መጠበቅ እና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግን ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሎጁ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ ሁለት የሄሊኮፕተር ማረፊያ፣ ከስድስት ሄክታር መሬት በላይ የሚሸፍን የሰው ሰራሽ ሐይቅ፣የአካባቢ ማስዋብ እና የደን ልማት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ህንጻዎች እና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በውስጡ ይዟል።
የ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የሚገነቡ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ማንሰራራት አይን ገላጭ ናቸው ብለዋል የፕሮጀክቱ አስተባባሪ።
የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ በአስደናቂ ታሪኳ፣ በተለያዩ መልክዐ ምድሮቿ እና ህያው ባህሏ የጉዞ መዳረሻ ሆና ይበልጥ እንድትደምቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የ‘ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ’ ለአካባቢው ማህበረሰብ ትርጉም ባለው መልኩ የስራ እድል እንደሚፈጥር እና ለዘላቂ ልማትና ብልጽግና የድርሻውን እንደሚወጣም ነው የገለጹት።