በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል እጩዎች ስም እና የመለያ ምልክት አደራደር ቅደም ተከተል የዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል እጩዎች ስም እና የመለያ ምልክት አደራደር ቅደም ተከተል የዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች ድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የስም እና የመለያ ምልክት አደራደር ቅደም ተከተል የዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ምርጫ መሪዎች የሚመረጡበት ብቻ ሳይሆን የጸጥታ አካላት ሙያዊ ብቃታቸውን በተግባር የሚያሳዩበት ነው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ቦርዱ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
በሂደቱም ከሲቪክ ማህበራት፣ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙሃን እና ጸጥታ አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎች ምዝገባ ተጠናቅቆ በየምርጫ ክልሎች የእጩዎች ስም ዝርዝር በይፋ መለጠፉን የተናገሩት ሰብሳቢዋ፣ለሚቀርቡ ቅሬታዎችም ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ ሲሆን፣ ከአራት ቀን በፊት በተደራጀ መረጃ መሰረትም ከ18 ሚሊየን በላይ ዜጎች ለመራጭነት መመዝገባቸውን አብራርተዋል።
የምዝገባ ሂደቱ በዲጂታል እና በማኑዋል እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ የሲስተም እና የኔትወርክ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ምዝገባው በማኑዋል እንዲካሄድ መደረጉን ገልጸዋል።
በ46 ሺ 757 የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁሶች መሰራጨታቸውንም ተናግረዋል።
በቦርዱ ከተመዘገቡ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 እጩዎች የቀረቡ ሲሆን 2 ሺህ 98 ዕጩዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆኑ 8 ሺህ 736 ደግሞ የክልል ተወካዮች መሆናቸው መገለጹ ይታወቃል።
73 እጩዎች ደግሞ በግል ለመወዳደር መመዘገባቸውም እንዲሁ።