ቀጥታ፡

ምርጫ መሪዎች የሚመረጡበት ብቻ ሳይሆን የጸጥታ አካላት ሙያዊ ብቃታቸውን በተግባር የሚያሳዩበት ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018 (ኢዜአ)፦ምርጫ መሪዎች የሚመረጡበት ብቻ ሳይሆን የጸጥታ አካላት ሙያዊ ብቃታቸውንና ገለልተኝነታቸውን በተግባር የሚያሳዩበት ወሳኝ መድረክ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ ገለጹ።

መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለአገር አንድነትና ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለፖሊስ መኮንኖች ያዘጋጀው የአመራር፣ የሰብአዊ መብቶች እና የምርጫ ደህንነት ስምሪት ላይ ያተኮረ ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል።


 

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ እንደገለጹት፤ ምርጫ መሪዎች የሚመረጡበት ብቻ ሳይሆን የጸጥታ አካላት ሙያዊ ብቃታቸውንና ገለልተኝነታቸውን በተግባር የሚያሳዩበት ወሳኝ መድረክ ነው።

በዚህም ቦርዱ በአሁን ወቅት ከፌዴራል፣ ከክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ፖሊሶችና የጸጥታ አካላት ጋር ተናቦ በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የምርጫ ጣቢያዎች ደህንነት ጥበቃ፣ የምርጫ ቁሳቁሶች የሚገኙበት ቦታ ደህንነት፣ የምርጫ ቁሳቁሶችን ከዋና መስሪያ ቤት ወደ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በማጀብ የማሰራጨት ስራ በትብብር እየተሰራ እንዳለ ጠቅሰዋል።

ምርጫው ፍትሐዊ እና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፖሊስ ድርሻ ቁልፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም በቂ ዝግጅት ሊኖረው እንደሚገባ ገልጸዋል።


 

በተለይም ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲኖር ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ ሚዛን ጠብቆ መሥራትና የዜጎችን መብቶች በሥርዓታዊ አግባብ እንዲከበሩ ማድረግ ከፖሊስ የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

የፖሊስ መኮንኖች በነፃነትና በገለልተኝነት ሥራቸውን በማከናወን የሕዝብ ፍላጎት በሙሉነት እንዲንጸባረቅና የዴሞክራሲ ሂደቱ እንዲጎለብት የበኩላቸውን ሚና እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ሥልጠናው በምርጫ ወቅት የሚፈጠሩ ሁኔታዎችን በብስለትና በብቃት ለመምራት ያግዛል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ታምራት ሙሉጌታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሥልጠናው በምርጫ ወቅት የጸጥታ አካላት ሊኖራቸው የሚገባውን ሙያዊ ስነ-ምግባር  ለማጠናከር ያስችላል ብለዋል።

ፖሊስ የሕዝብ ደህንነት ጠባቂ በመሆኑ በምርጫ ሂደት ውስጥ የዜጎችን ሰላማዊ የመንቀሳቀስና የመምረጥ መብት አክብረው እንዲሰሩ ስልጠናው ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም