መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለአገር አንድነትና ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለአገር አንድነትና ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፡- የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለአገር አንድነትና ለብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የልኅቀት ማዕከል የልዩ ትኩረት ዘርፍ ጋዜጠኝነት የመጀመሪያው ዙር ሠልጣኞች የማጠናቀቂያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለማንኛውም ዘገባ ብሔራዊ ጥቅምን ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ባለሙያዎች የሕዝብና የአገርን ጥቅም በዘላቂነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅመው፤ ለጠንካራ አገር እውን መሆን በአንድ ዓላማ መቆም ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ ረገድ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች አሰባሳቢ ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ባለሙያዎች ግጭትን ከሚያባብሱ ዘገባዎች ራሳቸውን ማራቅ እንዳለባቸው አሳስበው፤ ሙያዊ መርሆዎችን ተከትሎ መዘገብና መሥራት ከባለሙያዎች የሚጠበቅ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ በሠላምና መረጋጋት ዙሪያም ባለሙያዎች ቅድሚያ የሚሰጡት አጀንዳ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ እነዚህን ኃላፊነቶች በአግባቡ ለመተግበር የሚያስችል በቂ አቅም ሊኖራቸው እንደሚገባም አስታውቀዋል።
ጋዜጠኞች የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ የሚደረገው ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በልማት ረገድም የኢትዮጵያ ግቦች እንዲሳኩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውም ጠቅሰው፤ ሙስናን በተግባር ሊታገሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡