የትራንስፖርት ዘርፉን ከአካባቢ ብክለት የጸዳ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
የትራንስፖርት ዘርፉን ከአካባቢ ብክለት የጸዳ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፉን ከአካባቢ ብክለት የጸዳ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሐሰን ገለጹ፡፡
በባህር ዳር የአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያን ጨምሮ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው
ኢትዮጵያ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ መሰረተ ልማት፣በከተማ ትራንስፖርት እና አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ዘላቂ የትራንስፖርት ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራች ትገኛለች።
ይህንን ለመደገፍ ታዳሽ የኃይል ምንጭ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን ማስፋፋትና ዘርፉን ማበረታታት ከተሽከርካሪ የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ ለመቀነስ ያስችላል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሐሰን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዘርፉ አካባቢን እንዳይበክል ከማድረግ አኳያ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለሚያስመጡና ለሚገጣጥሙ አካላት አተገባበርን በተመለከተ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በዚህ ከቀረጥ ነጻን ጨምሮ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎች እየተደረገላቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
በነዳጅ የሚሰሩ ከሁለት እግር እስከ የከተማ ባስ እና የጭነት ተሽከርካሪዎች ድረስ ወደ ሀገር እንዳይገቡ ክልከላ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
ይህ እርምጃ ኢትዮጵያ ለዓለም የአየር ንብረት መጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
በአስር ዓመቱ ስትራቴጂ የልማት እቅድ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ500 ሺህ በላይ ተሽካርካሪዎች የታዳሽ ኃይል አማራጭን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ታስቦ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ታዳሽ የኃይል አማራጭን የሚጠቀሙ የተሽከርካሪዎች ቁጥር 115 ሺህ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የትራንስፖርት ዘርፉን ከአካባቢ ብክለት የጸዳ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አመላክተዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ፖሊሲ የትራንስፖርት ዘርፉ አካባቢን እንዳይበክል ከማድረግ ባሻገር ታዳሽ የኃይል አማራጭ ላይ ትኩረት እንዲደረግ እና የነዳጅ ጥገኝነትን ለመቀነስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ እንደ የነፋስ ኃይል፣ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የተፈጥሮ ጋዝ እና ሌሎች የታዳሽ ኃይል አማራጮች በስፋት መገኘት ከነዳጅ ተሽከርካሪዎች ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚደረገውን ሽግግር አስተማማኝ እንዳደረገው ጠቁመዋል፡፡