ጠንክሮ በመስራት ውጤታማ በመሆን ዓላማን ማሳካት ይቻላል-የማዕረግ ተመራቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
ጠንክሮ በመስራት ውጤታማ በመሆን ዓላማን ማሳካት ይቻላል-የማዕረግ ተመራቂዎች
ሰመራ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦ጠንክሮ በመስራት ውጤታማ በመሆን ዓላማን ማሳካት ይቻላል ሲሉ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የማዕረግ ተመራቂዎች ተናገሩ።
ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል
ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 987 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል በኘሮፌሽናል ኢዱኬሽን ትምህርት ዘርፍ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀው ተማሪ አደን ናስር አንዱ ነው።
ተማሪው ከዛሬ አጠቃላይ ተመራቂዎች 4 ነጥብ በማምጣት የሜዳሊያ እና የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
ተማሪ ናስር በወቅቱ በሰጠው አስተያየት፤ በዩኒቨርሲቲው የአራት ዓመት ቆይታው ለትምህርቱ ብቻ ትኩረት መስጠቱን ጠቁሞ ከተለፋና ከተደከመ ውጤታማ በመሆን ዓላማን ማሳካት ይቻላል ብሏል።
በቀጣይም ያስተማረውን አርብቶ አደር ማህበረሰብና ሀገርን በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቱንም ገልጿል።
ሌላኛዋ በዩኒቨርሲቲው በቢዝነስና ኢኮኖሚክሰ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 89 በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ተማሪ ላምሮት ጀግናው ናት።
ተመራቂዋ ባመጣችው ውጤት መደሰቷን ገልጻ ለውጤታማነቷ በዋናነት አስተዋጽኦ ላላቸው ለቤተሰቦቿ በተለይም ለእናቷ ምስጋና አቅርባለች።
ያስተማራትን ህብረተሰብና ሀገሯን በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቷንም ገልጻለች።
በዩኒቨርሲቲው የሥነ ዜጋና ሥነምግባር ትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 79 ውጤት በማስመዝገብ የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው አደን መሐመድ ነው።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ተግቶ በመማሩ ለውጤት መብቃቱን ገልፆ በቀጣይ ያስተማረውን ህብረተሰብና ሀገር በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ነው የተናገረው።