ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል
ሠመራ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት ዓመታት የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወኑ ተገለጸ።
ተመራቂዎች እየተከናወኑ በሚገኘው ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት የድርሻቸውን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 987 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃ መርሀግብሩ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታና የሰመራ የኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ስለሺ ግርማ እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት በአካባቢው ያለውን አርብቶ አደር ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል።
ምርምሮችን ጨምሮ ባከናወናቸው ተግባራት አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ተጠቃሚ እየሆነ እና ህይወቱ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የተግባር ተኮር ትምህርትን እውን ለማድረግ በሽግግር ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ስለሺ፣ ተቋሙ የትምህርት ጥራትን በማላቅ ባከናወናቸው ስራዎች ዘንድሮ መውጫ ፈተና ካስፈተናቸው ተማሪዎች መካከል 82 በመቶ አልፈው ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መሐመድ ኡስማን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ለሁለት አሥርት ዓመታት በአገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ አስተዋጽኦ ያለቸው ምሁራንን ማፍራቱን ተናግረዋል።
በዛሬ እለትም በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 987 ተማሪዎች እንዳስመረቀና ከእነዚህ ውስጥም 354ቱ ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዛሬው ምሩቃን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ባገኙት እውቀትና ክህሎት በቀጣይ ውጤታማ ሥራ በማከናወን ሀገርና ህዝብን ማገልገለ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዲጂታላይዜሽን አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ተቋማዊ አሰራርን እያላቀና በሲስተም የታገዘ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የመረጃ ሥርአቱንም በማዘመንና በተሻለ በማደራጀት የራስ ገዝ አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ በሂደት ላይ መሆኑንም ነው መሐመድ (ዶ/ር) የጠቆሙት።
ዩኒቨርሲቲው ከ100 በላይ የአርብቶ አደር ሴቶች ነጻ የትምህርት ዕድል መስጠቱንም ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው ተደራሽነቱን ለማሳደግ በክልሉ ባሉ አምስት የተለያዩ አካባቢዎችና በአማራ ክልል ባቲ ከተማ ቅርንጫፎችን ከፍቶ የመማር ማስተማር ስራውን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርምር ሥራዎቹን በማጠናከርም የልማት ስራዎችን እያገዘ መሆኑንም ተናግረዋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱ ሙሳን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።