በዞኑ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያን ማረጋጋት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያን ማረጋጋት ተችሏል
ደብረ ብርሃን፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያውን ማረጋጋት መቻሉን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
በክልሉ የዋጋ ንረትን ለማርገብ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ለሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራት ለምርት አቅርቦት እንዲሆን በመንግስት 208 ሚሊዮን ብር መመደቡ ምርቶችን በተሻለ ለማቅረብ አስተዋጽኦ ማድረጉም ተመልክቷል።
የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሀላፊ ተወካይ ፈጠነ ሞገስ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ የሚገኙ 41 የሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራት ከአርሶ አደሩ ጋር ትስስር በመፍጠር የግብርና ምርት ካለበት አካባቢ በማምጣት እጥረት ወደ ሚስተዋልበት የማቅረብ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
በዚህም አርሶ አደሮች ምርታቸውን በግብይት ማዕከላት አቅርበው ከመሸጥ ባለፈ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በቅርበት ለመግዛት መቻላቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ፈጠነ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ባለፉት 8 ወራት 470 ሺህ ኩንታል የግብርና እና 82ሺህ ኩንታል የኢንዱስትሪ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ በማቅረብ ገበያን የማረጋጋት ሥራ ተከናውኗል።
ለምርት አቅርቦቱ ከመንግስት ለህብረት ሥራ ማህበራት የተመደበው 208 ሚሊዮን ብርም ጤፍ፣ ስንዴ፣ ስኳር፣ የዳቦ ዱቄት፣ ዘይትና ሌሎች የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ አግዟል ብለዋል።
ፈጠነ (ዶ/ር) አክለው እንደገለጹት፣ በዘንድሮው የበጋ ወቅት በተካሄደ የመስኖ ልማት የተሳተፉ አርሶ አደሮች የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ በቂ ምርት ለገበያ እንዲቀርብ እያገዙ ነው።
ይህም ህብረተሰቡ ከኢድ አል ፈጥር በዓል በተጨማሪ መጪውን የትንሳኤ በዓል የሚፈልገውን የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የመስኖ አግሮኖሚስት ባለሙያ አቶ ዘሩ ገረመው በበኩላቸው እንዳሉት፤በመኸር እና በበጋ መስኖ የሰብል ልማት ምርታማነት ማደግ በቂ ምርት ወደ ገበያው ለማቅረብ አስችሏል።
በተያዘው የበጋ ወቅት እየተካሄደ ባለው የመስኖ ልማትም ስንዴና ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በማምረት ለገበያ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የተረጋጋ ግብይት እንዲኖር በማድረግ ሲስተዋል የነበረውን የዋጋ ንረት ለማርገብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።