በክልሉ የዋጋ ንረትን ለማርገብ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የዋጋ ንረትን ለማርገብ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ባህር ዳር ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የግብይት ማዕከላትን በማስፋፋትና የንግድ ሰንሰለትን በማሳጠር የዋጋ ንረትን ለማርገብ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።
በአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ እና በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የበጀት ድጋፍ የተገነባው የባህር ዳር ከተማ 2ኛ ደረጃ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ዛሬ ተመርቋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በክልሉ የገበያ ማዕከላትን በማስፋፋት የዋጋ ንረትን ለመከላከል አቅጣጫ ተቀምጦ በትኩረት እየተሰራ ነው።
የገበያ ማዕከላት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ግብይት እንዲያካሄድ የሚያስችሉ በመሆናቸው የማስፋፋት ስራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው ሲሉ አክለዋል።
የገበያ ማዕከላት አምራቹንና ሸማቹን ቀጥታ በማገናኘት ከደላላ ጣልቃ ገብነት የጸዳ የግብይት ስርዓት ለማዳበር ሚናቸው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ በርካታ የግብርና ምርት ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑን ገልጸው ተግባሩን አጠናክሮ በማስቀጠል የዋጋ ንረትን የማርገብ ስራ በልዩ ትኩረት ይከናወናል ብለዋል።
በባህር ዳር ከተማ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት በሆነው የገበያ ማዕከል የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች እንደሚቀርቡ ታውቋል።
በምረቃ ስነ-ሥርዓቱ ላይ የክልሉና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራር አካላትና አምራቾች ተገኝተዋል።