ቀጥታ፡

ፓርቲው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየሰራ ነው

አሶሳ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቤሕነን) ፓርቲ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የፓርቲው ሊቀመንበር አብዱሰላም ሸንገል ተናገሩ።

ፓርቲው የምርጫ ምልክቱን እና የምርጫ ማኒፌስቶውን ዛሬ ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ አስተዋውቋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳቦቻቸውን ለህዝብ ተደራሽ የሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል

የፓርቲው ሊቀመንበር አብዱሰላም ሸንገል በወቅቱ እንደተናገሩት፤ 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና ሠላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲያቸው በትኩረት እየሰራ ይገኛል።


 

ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ መካሄድ እንዳለበት ለፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሰራቱንም ጠቅሰዋል።

ፓርቲው ለክልል ምክር ቤት እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን በወቅቱ ማስመዝገቡን ጠቁመው፥ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ድምጽ ለመስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ በወቅቱ መውሰድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በፓርቲው ማኒፌስቶ ላይ የክልሉን ጸጋዎች በመጠቀም ህብረተሰቡን ያሳተፉ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን እና የህዝቦች ትስስርን ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ መቀመጡንም ተናግረዋል።

የፓርቲው የምርጫ ምልክት "የተጨባበጡ እጆች" እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም