ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳቦቻቸውን ለህዝብ ተደራሽ የሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል

ድሬዳዋ፤ መጋቢት 13/2018(ኢዜአ)፡- በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ ሀሳቦቻቸውን ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊና ሰላማዊ እንዲሆን የድርሻውን እየተወጡ መሆኑን የድሬዳዋ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት አስታወቀ።

የነጻ የአየር ሰዓት ድልድሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳባቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ ነው

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጣሂር ሮብሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዘንድሮ በሚካሄደው 7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርጅቱን የቴሌቪዥን እና የሬድዮ ጣቢያዎች ተጠቅመው አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦቻቸውን ለህዝብ ተደራሽ እያደረጉ ይገኛሉ። 

በጣቢያዎቹ ከተፈቀደላቸው የአየር ሰዓት በተጨማሪ የድርጅቱን የማህበራዊ ሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም በእኩልነትና በፍትሃዊነት ፖሊሲዎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ በ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እያካሄዱት ያሉትን የክርክር መድረክ ድርጅቱ ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ጀምሯል። 

ለእዚህም ገዢው ፓርቲን ጨምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማህበራዊና በምጣኔ ሃብት ጉዳዮች ላይ ያካሄዱት ክርክር ለህዝብ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

የፓርቲዎቹ አማራጭ ሀሳብ ለህዝብ ተደራሽ መሆን መራጮች በሚያገኙት መረጃ መሰረት ታግዘው ድምጻቸውን ለሚፈልጉት ፓርቲ እንዲሰጡ ያግዛል ብለዋል። 

እንደ አቶ ጣሂር ገለጻ፣ የድርጅቱ ጋዜጠኞችና የካሜራ ባለሙያዎች የምርጫ ህግን ተረድተውና  ሙያዊ ሥነ ምግባርን አክብረው በምርጫው የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ተከታታይ ስልጠና ተሰጥቷል።

የአቅም ግንባታ ስልጠናዎቹ በምርጫው የሚሳተፉ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በፍትሃዊነት እና በእኩልነት እንዲያገለግሉ ማስቻሉን ነው የተናገሩት። 

ፓርቲዎች በቀሪ ጊዜያት በድርጅቱ በተመቻቸውን የአየር ሰዓት ተጠቅመው ሃሳቦቻቸውን ለህዝብ ተደራሽ እንዲያደርጉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም