ቀጥታ፡

የጤና ምሩቃን ማህበረሰቡን በማገልገል ለጤናው ዘርፍ ግቦች ስኬት መስራት ይጠበቅባቸዋል

ሀዋሳ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦ የጤና ምሩቃን ማህበረሰቡን በሥነ ምግባርና በርህራሄ በማገልገል ለጤናው ዘርፍ ግቦች ስኬት መስራት እንዳለባቸው የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ሰላማዊት መንገሻ (ዶ/ር) ገለጹ።  

በእውቀት የዳበረ ትውልድ የማፍራት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሕክምና ዶክተሮችን ጨምሮ 427 የጤና ሳይንስ ተማሪዎችን አስመርቋል።


 

የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ሰላማዊት መንገሻ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ እንደሀገር የበለፀገ፣ ጤናማና አምራች ማህበረሰብ የመፍጠር ግብን ለማሳካት የጤና ባለሙያዎች ድርሻ የጎላ ነው።

በመሆኑም የዛሬ ተመራቂዎች ማህበረሰቡን በሥነ ምግባርና በርህራሄ በማገልገል ለሀገራዊ ግቦች ስኬት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የሕክምና ሙያ የሕሙማንን ስነ ልቦና ተገንዝቦ መስራትን ይጠይቃል ያሉት ሃላፊዋ ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን ክህሎት በተግባር በማረጋገጥ ሃገራዊና ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ 

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት ከ120 ሺህ በላይ ምሩቃንን በማፍራት ሀገራዊ ተልዕኮውን እየተወጣ ነው፡፡


 

በቀጣይ ዓመትም ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ የትምህርትና ምርምር ሥራዎችን አግባብነትና ጥራት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

ሀገር የተማሩ ዜጎቿን አንድነትና ትብብር የምትፈልግበት ወቅት ላይ ናት ያሉት ችሮታው (ዶ/ር) የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህም ተመራቂዎች በተመረቁበት የሙያ ዘርፍ ሃገራዊ ሃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ከዛሬ ተመራቂዎች መካከል 178 ሴቶች መሆናቸውን የጠቀሱት ደግሞ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍጹም ወልደገብርኤል (ዶ/ር) ናቸው።

ኮሌጁ ከመማር ማስተማር በተጨማሪ ሀገራዊ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በማህበረሰብ አገልግሎት በካንሰር ቅድመ ምርመራና ሕክምና፣ በጽኑና ድንገተኛ ሕክምና፣ በእናቶችና ህጸናት ሕክምና ትኩረት አድርጎ እየሰራም ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል። 

የሕክምና አገልግሎቶችን ጥራት በማሻሻልና በማዘመን ሃዋሳን የሕክምና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡


 

ከሕክምና ዶክትሬት ተመራቂዎቹ መካከል የወርቅ ተሸላሚው ዶ/ር ኤፍሬም ብዙአየው በበኩሉ፤ በረዥሙ የትምህርት ጉዞ ያሳየው ትጋትና ቁርጠኝነት ለውጤት እንዳበቃው ተናግሯል።

ወደስራው ዓለም ሲቀላቀልም ማህበረሰቡን በሙያዊ ስነምግባርና በውጤታማነት ለማገልገል መዘጋጀቱን ገልጿል።

 ከዛሬ ተመራቂዎች መካከል 88 በሕክምና ዶክትሬት፣ 268 በጤና ሳይንስ በመጀመሪያ ዲግሪ ፣ 70  በስፔሻሊቲ እንዲሁም አንድ ምሩቅ በሰብ ስፔሻሊቲ  መመረቃቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም