ቀጥታ፡

 በእውቀት የዳበረ ትውልድ የማፍራት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል 

ሀረር ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦ሀገሪቱ ለያዘችው የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት በእውቀትና በምርምር የዳበረ ትውልድ የማፍራት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ  የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ተመራቂ ተማሪዎች በቀሰሙት እውቀት ለሀገር የሚጠቅም ተግባር ሊያከናውኑ ይገባል

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ  በጤና የትምህርት ዘርፍ  በመጀመርያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 616 ተማሪዎች አስመርቋል።


 

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የእለቱ የክብር እንግዳ  ኦርዲን በድሪ በወቅቱ  ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሀገሪቱ ለያዘችው የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት የተማረ የሰው ሀይል በብዛትና በጥራት ማፍራት ወሳኝ ነው።

ለዚህም በእውቀትና በምርምር የዳበረ ትውልድ የማፍራት ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል።

ተመራቂዎችም  በዩኒቨርሲቲው ቆይታችሁ በፅንሰ ሀሳብ የቀሰማችሁትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ማህበረሰቡን ማገልገል ይገባችኋል ብለዋል።


 

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀማል ዩሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ዩኒቨርሲቲው ሀገሪቱ የሚያስፈልጋትን ጥራት ያለው የተማረ የሰው ሀይል በማፍራት ረገድ ግንባር ቀደም ሆኖ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅሙን በማሳደግ የመማር ማስተማር እንዲሁም የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎትን በስፋት እየሰጠ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

ተመራቂዎች ትውልድ የሚሻገር አስተዋጽኦ በማበርከት የሀገሪቱን  መጻኢ እድል ብሩህ ለማድረግ ሙያዊ ሀላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም