ተመራቂ ተማሪዎች በቀሰሙት እውቀት ለሀገር የሚጠቅም ተግባር ሊያከናውኑ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂ ተማሪዎች በቀሰሙት እውቀት ለሀገር የሚጠቅም ተግባር ሊያከናውኑ ይገባል
ቡሌ ሆራ ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦ ተመራቂ ተማሪዎች የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ለህዝብና ለሀገር እድገት የሚጠቅም ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ።
ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት መርሀ ግብሮች በአንደኛ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1 ሽህ 266 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሠራዊት ሀንዲሶ (ዶ/ር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት፤ በኢትዮጵያ አስተማማኝና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ በእውቀት፣ በክህሎትና በሥነ ምግባር የታነጹ ተማሪዎችን ማፍራት ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ።
የትምህርት ውጤታማነት በዋናነት የሚለካው ተማሪዎች የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ለማህበረሰብ እድገት ችግር ፈች መፍትሔ ሲያመነጩ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ተመራቂ ተማሪዎች የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ለህዝብና ለሀገር እድገት የሚጠቅሙ ተግባራት ሊያከናውኑ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በተለይም የአካባቢያቸውን ጸጋ ከሀገራዊ ብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር በማስተሳሰር ስራ ለመፍጠርና እራሳቸውን ለመለወጥ መጣር እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ተማሪዎችን ከብዙ ጥረት በኋላ ለምረቃ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ዩኒቨርስቲው የተልዕኮ ልየታውን የሚያግዙ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን የአካባቢው ጸጋ የማህበረሰብ የሃብት ምንጭ እንዲሆን እየተጋ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ተመስገን ደበሎ (ዶ/ር) ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር ዘርፍ በተለያዩ የትምህርት መርሀ ግብሮች ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያሰለጠነ መሆኑን አንስተው በዛሬው እለት ለ15ኛ ጊዜ በአንደኛ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 266 ተማሪዎች ማስመረቁን ተናግረዋል።
ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከባዮ ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል የሜዳልያ ተሸላሚ የሆነችው ሙስሊም ለማ በበኩሏ፤ በትምህርት ብቻ በማተኮር ተግታ በመስራቷ ውጤታማ መሆኗን ተናግራለች።
በቀጣይ የቀሰመችውን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ህዝብና ሀገርን ለመጥቀም እንደምትጥር ገልጻለች።
የቀሰመውን እውቀት በቅንነትና በታማኝነት በማካፈል ያስተማረውን ህብረተሰብ ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ያነሳው ደግሞ ከፋርማሲ ትምህርት ክፍል የሜዳልያ ተሸላሚ የሆነው ተሾመ አና ነው።