ቀጥታ፡

በምርጫው በንቃት በመሳተፍ የሚበጀንን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮልናል -አካል ጉዳተኞች

ወላይታ ሶዶ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ የሚበጀንን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮልናል ሲሉ የወላይታ ሶዶ ከተማ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ተናገሩ።

በምርጫው ድምጻችንን ለፈለግነው ፓርቲ ለመስጠት የሚያስችለንን ካርድ ወስደናል -የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች

ምርጫ ጣቢያዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ከመሆናቸው በላይ በቅርበት መገኘታቸው የምርጫ ተሳትፏቸውን እንደሚያሳድገውም ተናግረዋል። 

በወላይታ ሶዶ ከተማ የምርጫ ካርድ ሲወስዱ ኢዜአ ያነጋገራቸው አካል ጉዳተኞች እንደገለጹት በዘንድሮ ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱ በምርጫው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።


 

የወላይታ ሶዶ ከተማ አማኑኤል አካል ጉዳተኞች ማህበር መስራችና ሰብሳቢ አቶ መለሰ ኢዮብ የዘንድሮ ምርጫ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገና ያማከለ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ አካል ጉዳተኞች ካርድ ለመውሰድ እንዳይቸገሩ የምርጫ ጣቢያዎች በቅርበት መገኘታቸውና እነሱን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸው ለአካል ጉዳተኞች የተሰጠውን ልዩ ትኩረት ያሳያል ብለዋል።

በመጪው ጠቅላላ ምርጫ በመሳተፍ  ይጠቅመኛል፤ ሀገርንም በተሻለ ያስተዳድራል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ከወዲሁ ተመዝግበው ካርድ እንደወሰዱም ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ በላይ ጤቻ በበኩላቸው፤ የምርጫ ጣቢያዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው መዘጋጀታቸውና አካል ጉዳተኞች ቅድሚያ የሚስተናገዱበት ሁኔታም መፈጠሩ የምርጫ ተሳትፏችንን ያሳድገዋል ብለዋል።


 

በመሆኑም በተለይ ለአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት የተሻለ ሀሳብ ይዞ ለቀረበ ፓርቲ ድምጻቸውን በመስጠት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ለአካል ጉዳተኞች ተገቢ ትኩረት ባለመስጠት፣ በአመለካከት ችግርና ምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች  ምቹ ባለመሆኑ የምርጫ ተሳትፏችንን ገድቦት ነበር ያሉት ደግሞ አቶ ታረቀኝ ዛዛ ናቸው።


 

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እነዚህ ችግሮች ተወግደው ለአካል ጉዳተኛው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ አካል ጉዳተኛው መብቱን እንዲጠቀም ያደርጋል ያሉት አቶ ታረቀኝ፣ ለመራጭነት የሚያበቃ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውንም ተናግረዋል።

በምርጫው ቀን የተሻለ የፖሊሲ ሀሳብ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥም ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሀን የሚያደርጉትን ክርክር በሚገባ እየተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም