ቀጥታ፡

በምርጫው ድምጻችንን ለፈለግነው ፓርቲ ለመስጠት የሚያስችለንን ካርድ ወስደናል -የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች

ቦንጋ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦በጠቅላላ ምርጫው በንቃት በመሳተፍ ይበጀኛል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ መውሰዳቸውን የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የተሻለ ሐሳብ ያለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - የሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ የሚሰጥበት ቀን ነው።   

በአሁኑ ወቅትም የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረኮች በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን እየተካሄዱ ሲሆን መራጮችም ድምጻቸውን ለመስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ እየወሰዱ ይገኛሉ።

በቦንጋ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም ምርጫ ለአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባት መጠናከር ወሳኝ በመሆኑ በግንቦት ወር ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ይሆነኛል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የከተማው ነዋሪዎች መካከል መምህር አርጋው ዬራንጎ እንደገለጹት በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ድምጻቸውን ለፈለጉት ፓርቲ ለመስጠት ቀኑን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ለዚህም ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ መያዛቸውን የተናገሩት መምህሩ፣ ፓርቲዎች ከሚያደርጉት የሀሳብ ክርክር በመነሳት ለቀጣይ ሀገርን በተሻለ ይመራል፤ ዘላቂ ሰላምና ልማትንም ያስቀጥላል ያሉትን ፓርቲ እንደሚመርጡ ተናግረዋል።    

መምረጥ የሚቻለው ቀድሞ በመመዝገብ ካርድ መውሰድ ሲቻል እንደሆነ ገልጸው፣ ዕድሜው ለምርጫ የደረሰ ማንም ሰው በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ካርድ መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል። 

የከተማው ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አምሳለ ተፈራ፣ ምርጫ ሀገርን የሚያስተዳድር መንግስት በዴሞክራሲ መንገድ የሚመረጥበት በመሆኑ ትኩረት ሰጥተው በንቃት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።


 

እርሳቸውም ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ ከመውሰድ ባለፈ በአካባቢያቸው ሌሎችም ነዋሪዎች ካርድ እንዲወስዱ እየቀሰቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይ ሴቶች መብታቸውንና ጥቅማቸውን ከማስጠበቅ ባለፈ ሀገርን በሁሉም ዘርፍ የተሻለ ደረጃ ላይ ያደርሳል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በመለየት ድምጻቸውን እንዲሰጡና መብታቸውን እንዲጠቀሙ መክረዋል።

የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ በቴክኖሎጂ የተደገፈ መሆኑ ግልጽነትን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ያሉት ሌላው ነዋሪ አቶ ወርቁ ወልደሚካኤል በበኩላቸው፣ ለምርጫው ስኬታማነት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።


 

ለሀገርና ለህዝብ ጠቃሚ ሀሳብ አለው ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ በእጃቸው መያዛቸውን ጠቁመዋል።

በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብትን መጠቀም ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል ያሉት የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች፣ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ እንዲሆን የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም