ቀጥታ፡

ተመራቂዎች እየተከናወኑ በሚገኘው ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት የድርሻቸውን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል

ወልዲያ/ደብረ ብርሃን፤  መጋቢት 12/2018 (ኢዜአ)፦ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው በሀገሪቱ እየተከናወኑ በሚገኙ ሁለንተናዊ ልማቶች የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ተመላከተ።

ተመራቂ ተማሪዎቹ በበኩላቸው በተመረቁበት የሙያ ዘርፍ ህዝባቸውንና ሀገራቸውን በትጋት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አበበ ግርማ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀትና ክህሎት ሀገራችን እያከናወነች በምትገኘው ሁለንተናዊ ልማት የድርሻቸውን ማበርከት አለባቸው። 

ዩኒቨርሲቲው በማኔጅመንት፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ እና በጤናው ዘርፍ 2 ሺህ 388 ተማሪዎችን ማስመረቁን ተናግረዋል።

የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች ከመንግሥት ሥራ ባሻገር የፈጠራ ክህሎታቸውን በመጠቀም የሥራ ዕድል ፈጣሪዎች ሊሆኑ እንደሚገባም አሳስበዋል። 

ከዚህ ባሻገርም በአገራቸው ሰላምና ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ግንባር ቀደም ተሰላፊ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል። 

የማኔጅመንት ተመራቂው ጎበና ወንዴ በዩኒቨርስቲ ቆይታው ከቀለም ትምህርቱ ባሻገር የአንድነትና የመከባበር ባህልን ለማዳበር አስችሎኛል ብሏል። 

በተመረቀበት የሙያ ዘርፍም ሃገሩንና ህዝቡን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቱን ተናግሯል።

''ሙያዬ ከቴክኖሎጂ ዓለም ጋር ያዛመደኝ በመሆኑ ውጤታማ ስራ ለመስራት ትልቅ ተስፋ አድርጌያለሁ'' ያለችው ደግሞ በአይሲቲ ሙያ የተመረቀችው መስከረም አባተ ናት። 

ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዕቅድ ስኬት ላይ የበኩሏን  ለመወጣት ስልጠናው ጥሩ አጋጣሚን እንደፈጠረላትም ገልጻለች። 

በተመሳሳይም  የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸው 1 ሺህ 800 ተማሪዎችን በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ አስመርቋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስማረ መለስ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ተመራቂዎች ያስተማራቸውን ማህበረሰብ በልማት፣ በሰላምና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ችግር ፈቺ ተግባራትን በማከናወን ሊያግዙ ይገባል።

በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው በአዳዲስ ቴክኖሎጂ በተደገፈ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ትምህርታቸውን ወስደው በተሻለ ብቃት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

ዛሬ ለምረቃ የበቁት በተለያዩ የትምህርት መስኮች 1 ሺህ 800 ተማሪዎች ሲሆኑ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል።

የዩኒቨርስቲው የቦርድ አባል አርቲስት አበበ ባልቻ እንዳለው፤ ተመራቂዎች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም በጥናትና ምርምር የታገዘ ችግር ፈቺ ተግባራትን ሊያከናውኑ ይገባል።

በህክምና ላቦራቶሪ በከፍተኛ ውጤት የተመረቀው ቢተውልኝ ደባስ እንዳለው፤ በቆይታው ባገኘው እውቀት ሃገሩንና ህዝቡን በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቱን ተናግሯል።

ያስተማራትን ማህበረሰብ በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቷን የገለፀችው ደግሞ በከፍተኛ ውጤት የተመረቀችው  ውዴ መላኩ ናት።

በዩኒቨርስቲዎቹ ምረቃ ስነ-ስርዓቱ ተመራቂዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም