የልማት ጥያቄያችን ምላሽ እያገኘ በመሆኑ ተደስተናል−የደቡብ ኦሞ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የልማት ጥያቄያችን ምላሽ እያገኘ በመሆኑ ተደስተናል−የደቡብ ኦሞ ዞን ነዋሪዎች
ጂንካ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦የብዙ ዓመታት የልማት ጥያቄያቸው ምላሽ እያገኘ በመምጣቱ መደሰታቸውን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደቡብ ኦሞ ዞን ሳላማጎ ወረዳ የሀና ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
በማጎ ብሔራዊ ፓርክ እና በኦሞ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት አካባቢ የምትገኘው የሀና ከተማ ከአዲስ አበባ ወደ 900 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
ድሬዳዋን ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል--ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ
የሀና ከተማ በዙሪያዋ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 እና 2 ፕሮጀክት እንዲሁም ሰፋፊ የግል ኢንቨስትመንቶች የሚገኝባት ስትሆን ሰሊጥ እና ማሾም በአካባቢው በስፋት ይመረታል፡፡
ከተማዋ ዕድሜ ጠገብ ብትሆንም ዕድገቷ የዕድሜዋን ያህል አለመሆኑ ግን በነዋሪዎቿ ዘንድ ቅሬታን ሲፈጥር ቆይቷል።
የንጹህ መጠጥ ውሃ ፣ የኤሌክትሪክና እና ደረጃውን የጠበቀ የአስፋልት መንገድ በነዋሪዎች ዘንድ ለዘመናት ሲነሱ የነበሩ የልማት ጥያቄዎች ናቸው።
መንግስት ጥያቄዎችን ሰምቶ ያስጀመረው የ3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ በጥሩ ሂደት ላይ መገኘቱ ተስፋቸውን እንዳለመለመው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አመለወርቅ ካሱ፤ የከተማዋ ልማት አለመፋጠኑ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
የለውጡ መንግስት ለልማት ጥያቄያቸው ትኩረት ሰጥቶ ከተማዋን ከሌሎች ከተሞች እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ ደረጃውን የጠበቀ የአስፋልት መንገድ በማስጀመሩ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሌላው የሀና ከተማ ነዋሪና በጡረታ የሚተዳደሩት ሜጀር ጄኔራል አለሙ አየነ በበኩላቸው፤ ከተማዋ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ምቹ እንደሆነች ጠቁመው፣ ልማቷን ማፋጠን ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
ከህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አንዱ ምላሽ በማግኘቱ ተስፋቸው መደሰታቸውን ገልፀው፣ በቀጣይም የንፁህ መጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ ጥያቄያቸው ምላሽ እንደሚያገኝ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
በከተማዋ ቀደም ሲል የነበረው የሰላም እጦት ለእድገቷ ችግር ፈጥሮ እንደነበር የገለጸው ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ኤርስ ባባይቴ ነው።
የሀና ከተማ እንደ ሌሎች ከተሞች የልማት ተጠቃሚ እንድትሆን የአካባቢው ወጣቶች ህዝብን ለልማት በማስተባበር የበኩላቸውን እየተወጡና ከወረዳው አመራሮች ጋርም በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሀና ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ደበበ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ማዘጋጃ ቤቱ የከተማዋን ነዋሪዎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየሰራ ይገኛል።
በከተማው የኮሪደር ልማት አካል የሆነው 3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአስፋልት መንገድ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም ግንባታው 80 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።
የአስፋልት መንገዱን በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ፀጋዬ፣ በቀጣይም የአረንጓዴ ልማት፣ የእግረኛ መንገድ፣ አደባባይ የማስዋብና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ለማከናወን መታቀዱን ገልጸዋል።
የሀና ከተማን ለቱሪዝምና ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ተመራጭና ውብ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም የገለጹት ደግሞ የሣላማጎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ህጉ ቅጣቴ ናቸው።
የህዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለማሟላት በመንግስት ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው፣ በከተማዋ የተጀመረው መሰረተ ልማትን የማሟላት ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።