የነጻ የአየር ሰዓት ድልድሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳባቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የነጻ የአየር ሰዓት ድልድሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳባቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2018(ኢዜአ)፦ የነጻ የአየር ሰዓት ድልድሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳባቸውን በነፃነት ለህዝብ የሚያስተዋውቁበት መድረክ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ንዋይ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በፖለቲካ ፓርቲዎች የነጻ የአየር ሰዓት ድልደላና አጠቃቀም ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
አቶ ተስፋዬ ንዋይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የነጻ የአየር ሰዓት ድልድሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ መወዳደሪያ ፖሊሲያቸውን ለህዝብ የሚያስተዋውቁበት መድረክ ነው።
ቦርዱ ከመገናኛ ብዙኅን ባለስልጣን ጋር መመሪያ በማዘጋጀት የተተገበረው የነጻ አየር ሰዓት ድልድል ለምርጫው ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሕዊነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እስካሁን ድረስ ከ18 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የድምፅ መስጫ ካርድ መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።
በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመደበላቸውን የነጻ አየር ሰዓት በመጠቀም የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ ማቅረብ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ሰለሞን ታፈሰ፤ የነጻ አየር ሰዓት ድልድል ሥርዓቱ በምርጫ ፉክክር ሂደቱ የፖሊሲ አማራጮቻችንን በፍትሕዊነት ለህዝብ ለማቅረብ ጉልህ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ አባል ከማል ሰዒድ፤ የነጻ የአየር ሰዓት ድልድሉን በመጠቀም የፖሊሲ አማራጭ ሃሳቦች ለህዝብ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል።
የወሎ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀ መንበር ነጻነት ጣሰው በበኩላቸው፤ የድልድል ሥርዓቱ ህዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የፖሊሲ ሃሳብ በዕውቀት ላይ ተመሰረቶ ድምፅ እንዲሰጥ ያስችላል ብለዋል።
የዶንጋ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀ መንበር ዓለሙ ከበደ፤ ድልድሉ በምክክርና ግልጽ መስፈርት መደረጉ የምርጫ ሂደት መተማመንን የሚያጎለብት ወሳኝ አሰራር መሆኑን ተናግረዋል።
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ደምሴ ስኳሬ፤ የፖሊሲ አማራጭ መፎካከሪያ የአየር ሰዓት ድልድሉ ዴሞክራሲዊ የምርጫ ባህልን ለማጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አንሰተዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ግዛው ተስፋዬ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመደበላቸውን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ በአግባቡ መጠቀም እደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
መገናኛ ብዙሃንም የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጫቸውን ለህዝብ የሚቀርቡበትን የአየር ሰዓት ሙያዊ ገለልተኝነትና ሚዛናዊነትን በማስጠበቅ ለሃሳብ የበላይነት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የነጻ የአየር ሰዓት ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች 40 በመቶ፣ ባስመዘገቡት ዕጩዎች ብዛት 25 በመቶ፣ የሴት ዕጩዎች 15 በመቶ፣ አካል ጉዳተኞች 15 በመቶ እና ሴት አካል ጉዳተኞች 5 በመቶ ባስመዘገቡት መሠረት የሚደለደል መሆኑን ተገልጿል።