ቀጥታ፡

የካራባኦ ካፕ ዋንጫን ማን ያነሳል? አርሰናል ወይስ ማንችስተር ሲቲ? 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2018 (ኢዜአ)፦ አርሰናል እና ማንችስተር ሲቲ በእንግሊዝ ካራባኦ ካፕ ዛሬ የሚያደርጉት የፍጻሜ ጨዋታ ይጠበቃል።

ጨዋታው ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ 90 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ዌምብሌይ ስታዲየም ይካሄዳል።

242ኛው የማድሪድ ደርቢ

በግማሽ ፍጻሜው አርሰናል ቼልሲን፣ ማንችስተር ሲቲ ኒውካስትል ዩናይትድን በደርሶ መልስ ውጤት በማሸነፍ ለፍጻሜው ጨዋታ ቀርበዋል። 

አርሰናል የካራባኦ ዋንጫን ሁለት ጊዜ አንስቷል። መድፈኞቹ ለመጨረሻ ጊዜ ውድድሩን ያሸነፉት እ.አ.አ በ1992/93 የውድድር ዓመት ነበር።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ ዋንጫን ካነሳ 33 ዓመታት ተቆጥረዋል።

ተጋጣሚው ማንችስተር ሲቲ ስምንት ጊዜ ውድድሩን በማሸነፍ ከሊቨርፑል (10 ዋንጫ) ቀጥሎ ስኬታማው ክለብ ነው።

ውሃ ሰማያዊዎቹ ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫውን ያነሱት እ.አ.አ በ2020/21 የውድድር ዓመት ነበር።

ሁለቱ ክለቦች በካራባኦ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ማንችስተር ሲቲ አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አርሰናል በሁለት ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል።

በጨዋታዎቹ ላይ ማንችስተር ሲቲ 12 ግቦችን ሲያስቆጥር አርሰናል አራት ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። 

እ.አ.አ በ2020/21 በሩብ ፍጻሜው በተገናኙበት የመጨረሻ የእርስ በእርስ ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ 4 ለ 1 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፏል። ለፍጻሜ ደርሶም ዋንጫውን አንስቷል።

ሁለቱ ቡድኖች በካራባኦ ዋንጫ ፍጻሜ ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

እ.አ.አ በ2017/18 በፍጻሜው ተገናኝተው ማንችስተር ሲቲ 3 ለ 0 አሸንፎ ዋንጫውን አንስቷል።

አርሰናል ለመጨረሻ ጊዜ ማንችስተር ሲቲን በካራባኦ ዋንጫ ያሸነፈው እ.አ.አ በ2004/05 ነው።

በወቅቱ አርሰናል በአራተኛው ዙር 2 ለ 1 አሸንፏል።

ማንችስተር ሲቲ በካራባኦ ዋንጫ በአርሰናል ላይ የበላይነት አለው።

አርሰናል የካራባኦ ዋንጫን ለሶስተኛ ጊዜ ለማሸነፍ፣ ማንችስተር ሲቲ ለዘጠነኛ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት ይጫወታሉ።

አርሰናል አራት ዋንጫዎችን ለማንሳት እየተፎካከረ ነው።

በሳምንቱ አጋማሽ ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የተሰናበተው ማንችስተር ሲቲ ለሶስት ዋንጫ እየተጫወተ ይገኛል።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አርሰናል አንደኛ፤ ማንችስተር ሲቲ ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ቡድኖቹ ዘንድሮ የመጀመሪያ ዋንጫ ለማንሳት የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው።

የ43 ዓመቱ ፒተር ባንክስ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም