242ኛው የማድሪድ ደርቢ - ኢዜአ አማርኛ
242ኛው የማድሪድ ደርቢ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2018(ኢዜአ)፡- በስፔን ላሊጋ የ29ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ዛሬ የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የካራባኦ ካፕ ዋንጫን ማን ያነሳል? አርሰናል ወይስ ማንችስተር ሲቲ?
ጨዋታው ከምሽቱ አምስት ሰዓት 84 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው በርናባው ስታዲየም ይካሄዳል።
ሪያል ማድሪድ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 28 ጨዋታዎች 21ዱን ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ ላይ 60 ግቦችን ሲያስቆጥር 24 ጎሎችን አስተናግዷል።
ማድሪድ በ66 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው አትሌቲኮ ማድሪድ 28 ጨዋታዎችን አድርጎ በ17ቱ ድል ሲቀናው በአምስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። ስድስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
57 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 47 ጎሎች ተቆጥሮበታል። አትሌቲኮ በ57 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የማድሪድ ከተማ ክለቦቹ በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የዛሬው ለ242ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ በፊት ባደረጓቸው የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ 117 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።
አትሌቲኮ ማድሪድ 61 ጊዜ አሸንፏል። 63 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ባላንጣ ክለቦች በላሊጋው እስከ አሁን 177 ጊዜ ተገናኝተው ሪያል ማድሪድ 91 ጊዜ አሸንፏል። አትሌቲኮ ማድሪድ 42 ጊዜ ሲያሸንፍ 44 ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
ሪያል ማድሪድ ማሸነፍ በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
የከተማ ተቀናቃኙ አትሌቲኮ ማድሪድ ካሸነፈ ከሪያል ማድሪድ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስድስት ዝቅ ያደርጋል።
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድ 5 ለ 2 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
የ42 ዓመቱ ሆዜ ሉዊስ ሙኑኤራ ሞንቴሮ የደርቢውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በተያያዘም በ70 ነጥብ ሊጉን የሚመራው ባርሴሎና ከቀኑ 10 ሰዓት ከራዮ ቫዮካኖ ጋር በካምፕኑ ስታዲየም ይጫወታል።