ቀጥታ፡

ተከፍሎ የማያልቅ የኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ውለታ አለብን - የመናዊያን ፍልሰተኞች

በዮሐንስ ደርበው 

ምድረ ቀደምቷ ሀገር ኢትዮጵያ ለተገፉ፣ ጥላ ከለላ ለሚሹ፣ ለተከዙና ለታረዙ የሀገራት ዜጎች መጠጊያ ናት። የኢትዮጵያን ቸርነትም ከተጠለሉባት እንግዶቿ በላይ ምሥክር የለም።

የኢትዮጵያን ደጅ የረገጡ ሁሉ በቆይታቸው ለተደረገላቸው ሁሉ ‘ውለታችንን በምን እንክፈል’ ሲሉ ይደመጣሉ። ከአያሌ ሀገራት በመልከ ብዙ ቀውሶች ሳቢያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሁሉ የቆሰሉ ልባቸው ታክሞ፣ ዕንባቸው ታብሶና ሕይወታቸው ታድሶ ኑራቸውን አደላድለዋል። 

የብርቱዎቹ ልጆች ብርታት በቀጣይ ...!

በዚህም ከአፍሪካም ሆነ ከተቀረው ክፍላተ ዓለም የጦርነትና ግጭት ጥላ ያጠላባቸውና ሰላምን የተጠሙ የቀጣናው ሀገራት ዜጎች ኢትዮጵያን ሲሹ ማየት የተለመደ ነው።

 የየመን ዜጎች ለዚህ ማሳያ ናቸው።  ኢብቲሳም ኻሊድ እና መሰል የመናዊያን ከየመን የእርስ በርስ ግጭት በኋላ የኢትዮጵያን ደጅ ረግጠው ዛሬ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሚተርፍ የተድላ ኑሮ እየኖሩ ነው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረገችው ኢብቲሳም እንደምትለው፤ በየመን አለመረጋጋት በፈጠረው ጠባሳ እርሷና መሰሎቿ ለፍልሰት ተዳርገዋል። ለዚህ ደግሞ ምርጫቸው ኢትዮጵያ ሆነች። ወደ ኢትዮጵያም መጥተው የሀገሬው ፊት ሳይኮሰኩሳቸው በፍቅር እንደተቀበሏቸው ትናገራለች። በዚህም ዛሬ የመናዊያን ተስፋቸው ለምልሞ፣ ሕይወታቸው ሠምሮ ኢትዮጵያን እንደ እናት ቆጥረው እየኖሩ ስለመሆኑ ትናገራለች።

ከ11 ዓመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ኢብቲሳም፤ በወቅቱ ቀኑ እንደጨለመባት ታወሳለች። ሰው ከቤቱ፣ ከወገኑ…ከሀገሩ ወጥቶ ወዴት ይሄዳል? በወቅቱ የነበረውን ጭንቀት ማየልም ታስታውሳለች።

አሁን ግን ስለ ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ በጎነት ዐውርታ አትጠግብም። “አሁን ፍልሰተኛ አይደለሁም፤ ያለሁት በሁለተኛዋ ሀገሬ ኢትዮጵያ ነውና” ትላለች።

እንዲህ ባለው የረመዳን ወቅት ደግሞ የፍልሰተኞች ሁሉ ሰብሳቢ ናት። “ሁሉም ከእነ ቤተሰቡ ወደ ቤቷ እየመጣ ያፈጥራል። በዚህም በፍልሰት እንደመጡ ሳይሆን ቤተሰባዊነት ይሰማቸዋል። ከየመን፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ አፍጋኒስታን፣ ኮንጎሊዝ (DRC) ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሁሉ ሰብሰብ ብለው የኢፍጣር መርሐ-ግብርን እንደሚያከናውኑም ታነሳለች።

በዚህ ላይ ኢትዮጵያውያን ብርታት ናቸው ትላለች፤ ሁሌም ‘አይዟችሁ፣ በርቱ፣ ነገ ጥሩ ይሆናል’ እያሉ ያበረቱናል፤ ክብርና ፍቅር ይሰጡናል ስትልም ታስረዳለች።

የኢትዮጵያንና ሕዝቧን ውለታ እንዴት መክፈል ይቻላል? ኢትዮጵያን ሀገራችን ብለን ነው እየጠራን ያለነው። እንደ እንግዳ እንደ ፍልሰተኛ እራሳችንን አናስብም፤ እንደሀገሬው አንዱ እንጅ፤ የምትለው ኢብቲሳም፤ ኢትዮጵያን እንዴት ብዬ ነው የምገልጻት? እናትን መግለጽ ይቻላል? እናትን መግለጽ ከተቻለ ኢትዮጵያን በዚያ ልክ መግለጽ ይቻል ይሆናል፤ እኔ ግን አይቻለኝም በማለት ትናገራለች።

“የዛሬ 11 ዓመት ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት፤ የሰው ፊት አልገረፈኝም፤ ፊቱን ያዞረብኝም የለም።

ኢትዮጵያውያን ደግ፣ ቅንና ደስ የምትሉ ሕዝቦች ናችሁ” ስትል ስሜቷን ትገልጻለች።

ኢትዮጵያ እንደ ኒውዮርክ እያደገች ነው፤ እኛ ከመጣን በኋላ እንኳን በርካታ ለውጦች ዕያየን ነው ስትልም የኢትዮጵያን የለውጥ ሂደት አንስታለች።

ለአብነትም ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በርካታ ነገሮች መስተካከላቸውን በመጠቆም፤ ለዚህም የኢትዮጵያን መንግሥት እናመሠግናለን ብላለች። ከፍልሰተኞች ጋር በተያያዘ በርካታ ሕጎች በመሻሻላቸው፤ ዛሬ በራሴ ስም ንግድ ፈቃድ አውጥቼ እየሠራሁ ነው፤ በጨረታዎችም እወዳደራለሁ፤ የበጎ አድራጎት ማኅበር መመሥረትና መምራት ችያለሁ። እነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ያመጣቸው ለውጦች ናቸው ብላለች።

በምድረ ኢትዮጵያ ያለን ሁሉ ለኢትዮጵያ ዕድገት እንተባበር ስትልም ጥሪ አቅርባለች። ህልማችን ከኢትዮጵያውያን ጎን ሆነን ኢትዮጵያን በማሳደግ ጥረት በንቃት መሳተፍ ነው፤ የኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ውለታ መመለስ አለብን ስትልም ትናገራለች።

በኢብቲሳም ኻሊድ ቤት በተዘጋጀ የኢፍጣር መርሐ-ግብር ላይ የተሳተፈው አነስ አንዋር ለኢዜአ እንዳለው፤ ኢትዮጵያ በሯን ከፍታ አስጠልላዋለች። 

ከተለያዩ ሀገራት ብንመጣም ሰብሰብ ብለን ስናፈጥር፤ ማኅበራዊና ቤተሰባዊነታችን ይጠናክራል ብሏል። 

ብዙ ፈተናዎችን ዐይተናል፤ አልፈናቸው እዚህ ደርሰናል የሚለው አነስ፤ “ኢትዮጵያዊነት መልካምነት ነው” ሕዝቡ በክብር ነው የተቀበለን፤ ከምሥጋና ውጭ ምን ማለት እንችላለን? አመሥጋኞች ነን ሲል ገልጿል።

እየተማርኩ ነው፤ ትምህርቴን አጠናቅቄ በሙያዬ በመሠማራት ኢትዮጵያን ማገዝ እፈልጋለሁ ብሏል። 

ራኪያ አሊ አብዱረዛቅ በበኩሏ በፈረንጆቹ 2011 ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷን ታወሳለች። ትምህርቷንም ተከታትላ መመረቋን ገልጻ፤ ቤተሰብ አፍርታ ሁለት ልጆችንም ወልዳ እየኖረች ነው።

ኢትዮጵያ ሁለተኛ ሀገሬ ናት፤ ሰላም አላት፤ ሕዝቡም ሰው አክባሪ ነው። ለኢትዮጵያ የተሻለ ልማት ደግሞ መተባበር ወሳኝ ስለሆነ ለዚሁ እንትጋ ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።

#ፍልሰተኞች  #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም