ቀጥታ፡

ጠቅላላ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊና ቅቡልነት ያለው እንዲሆን የጋራ ምክር ቤቱ ሚናውን ይወጣል

ሀዋሳ፤ መጋቢት 10/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ቅቡልነት ያለው እንዲሆን የምክር ቤቱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸውን እንደሚወጡ የሲዳማ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር እና ቅስቀሳ አማራጭ ሀሳቦች የሚቀርቡበት ሊሆን ይገባል - ምሁራን

የጋራ ምክር ቤቱ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በሀዋሳ ከተማ አካሂዷል።


 

የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ በለጠ ሰጌቦ በመድረኩ እንደገለጹት፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያለው እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና የጎላ ነው።

በክልሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ምቹ የፖለቲካ ምህዳር መኖሩን ጠቅሰው በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታዎች አሉ ብለዋል።


 

በዚህም ተአማኒነት ያለው፣ ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ሚናችንን እንወጣለን ብለዋል።

የምርጫ ሥነ ምግባር ህጉን በተከተለ መንገድ አማራጭ ሃሳቦችን በማቅረብ የጋራ ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ለዚህም በምርጫው በሰላማዊ መንገድ ከመንቀሳቀስ ባለፈ የህዝቡን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ህዝቡ ለመራጭነት የሚያበቃውን ካርድ እንዲወስድ ማነቃቃት ይገባል ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሃላፊና የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ኤርሚያስ በበኩላቸው፤ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ እንዲሆን የጋራ ምክር ቤቱ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።


 

የጋራ ምክር ቤቱ ለዴሞክራሲያዊ ሥርአትና ለመድብለ ፓርቲ ግንባታ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ ለምርጫው ስኬታማነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃላፊነታችንን እንወጣለን ነው ያሉት።

የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ፤ መድረኩ በመጪው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸውን በአግባበ እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ምርጫው ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ላይ ያተኮረ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሀገር አቀፍና በክልል አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ 23 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም