ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር እና ቅስቀሳ አማራጭ ሀሳቦች የሚቀርቡበት ሊሆን ይገባል - ምሁራን

ሚዛን አማን፤መጋቢት 9/2018  (ኢዜአ) ፡-የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያካሂዱት ክርክር እና ቅስቀሳ አማራጭ የፖሊሲ ሀሳቦች የሚቀርብበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ምሁራን ተናገሩ።

ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በግንቦት ወር መጨረሻ ለማካሄድ የተለያዩ የቅድመ ምርጫ ሥራዎችን እያከናወነች ሲሆን  የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክርና ቅስቀሳ መርሃ ግብርም እየተካሄደ ነው።

በዚህ መሰረትም የተለያዩ ሀገር አቀፍና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሀንና በተለያዩ አማራጮች ያሏቸውን አማራጭ የፖሊሲ ሀሳቦች በማንሳት ክርክርና ቅስቀሳ እያካሄዱ ነው።

በዚህ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንደገለጹት ምርጫ የአንድ ሀገር ትልቁ የዴሞክራሲ ሥርአት መገለጫ መሆኑን ገልጸው፤ ፍትሐዊና፣ ነጻ፣ ተአማኒና አካታች እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን  መወጣት አለበት ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም በምርጫ ወቅት በሚያደርጓቸው ክርክሮችና ቅስቀሳዎች ለመመረጥ ያስችለናል ያሏቸውን የፖሊሲ አማራጮች ህዝብን ባከበረ መልኩ ማቅረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል።  

በተለይ ብሔራዊ አንድነትን የሚያስጠብቁ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፣ በመከባበርና በመቻቻል አማራጭ ሃሳባቸውን አቅርበው የህዝብን ስነ ልቦና በጠበቀ መልኩ መከራከር እንዳለባቸው መክረዋል። 

በዩኒቨርሲቲው የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት መምህር ሙሉቀን አየለ በበኩላቸው እንዳሉት በቅድመ ምርጫ ወቅት የሚከናወኑ የክርክርና የቅስቀሳ ሂደቶች የፓርቲዎች ማንነት የሚለይበት ነው።

በመሆኑም መንግሥት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ፣ ሲከራከሩና የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የመራጩን ሕዝብ ሞራልና ሥነ ልቦና ሊጠብቁ ይገባል ብለዋል።

የምርጫ ሥነ ምግባርን በመከተልና የተሻለ አማራጭ ሀሳብ በማቅረብ የነገዋን ኢትዮጵያ አጉልቶ ማሳየት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል ሚዛናዊ አቋም ይዘው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሏቸውን የፖሊሲ አማራጮች የምርጫ ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ ከፍ አድርገው ማዘጋጀትና ማቅረብ አለባቸው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ቢመርቅ በሪሁን ናቸው።

ምርጫ የውድድር ሜዳ ሊሆን የሚችለው ተነጻጻሪ የሆኑ ጠንካራ ሀሳቦች ሲቀርቡበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ፓርቲዎች በተሻለ መልኩ ለመሥራት መዘጋጀታቸውን የሚያሳይ ሀሳብ ማቅረባቸው መራጩ ሕዝብ የሚፈልገውን ለመምረጥ ያስችለዋል ብለዋል።

ፓርቲዎች ለአንድ ሀገር እንደመሰራታቸው መጠን መከባበርና መቻቻልን መርህ አድርገው ሊንቀሳቀሱ ይገባል ያሉት መምህሩ፣ የመመረጥ ዕድላቸውን ለማስፋት የምርጫ ሕግና ሥርዓትን መከተል እንዳለባቸው አክለዋል።

ብሔራዊ አንድነትን በሚያስጠብቁ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ሊሰሩ እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል።

እስካሁን በመገናኛ ብዙሀን ለክርክር የተመቻቸው መድረክ በአንጻራዊነት የተሻለ መሆኑን ገለጸው አካታችነትን በጠበቀ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም